Soap made from Dirt Can’t Remove Dirt: Are You Journalist or Racist?

by Bekahegn

ከቆሻሻ ቅመም የተሰራ ሳሙና እድፍን እንደማያፀዳ ሁሉ የሰው ልጆችን እኩልነት የማይቀበል አዕምሮ ስለአንድነት ሊሰብክ አይችልም
ይድረስ ለዘረኛ ጋዜጠኞች፣ የህዝብ የመገናኛ ሚዲያ ተቋማት ግለሰቦች እና ቡድኖች በሙሉ
ጎንደር
ኢትዮጵያ የብዙ ብሄር ብሄረሰቦች መኖሪያ፣ የተለያዩ ቋንቋዎች የሚነገርባት ፣ ብዝሀ ባህሎች የሚንፀባረቅባት፣ የተለያዩ ሀይማኖቶች የሚመለኩባት አገር ትሁን እንጅ እነዚህ የተለያየ ቋንቋ፣ ባህል እና እምነት ያላቸው ህዝቦች ለዘመናት ራስ ወዳድ በሆኑ ገዥዎች የተለያዩ ግፍና መከራን ተቀብለዋል፡፡ ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨትና የውጭ አገር ወራሪዎች እንደሚያደርጉት ሁሉ በከፋፈለህ ግዛው (divide and rule) የፖለቲካ መርዝ በመንደፍ አንደኛውን ህዝብ ሰው ሰራሽ (artificial) ማንነት በማላበስ ‹‹የበላይ ነኝ›› ብሎ እንዲታበይ(become hypocritical) እና ሌላውን ደግሞ የበታችነት ስሜት እንዲሰማው የተለያዩ ስሞችን መስጠት ዋነኛ እኩይ ተግበራቸው ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ወንድም ወንድሙን እንዲያሳድድ፣ በንቀት እና በበታችነት እንዲመለከተው በማድረግ አንድ አና ተመሳሳይ ህዝቦች በጠላትነት እንዲተያዩ እና እንዲጠፋፉ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ እነዚህ እፉኝት ገዥዎች ስልጣናቸውን ለማራዘም ሲሉ በህዝቦች መካከል የረጩት መርዝ በመጠኑም ቢሆን ወንድማማች ህዝቦች በጠላትነት እንዲተያዩ ለማድረግ ቢሞከሩም በአብዛኛው ግን አልሰራላቸውም፡፡ ኢትየጵያዊያን የገዥዎቻቸውን መርዝ በማርከስ ሁሉም ህዝቦች ዘመን ተሸጋሪ የሆነ አንድነታቸውን በተለያየ ወቅት አስመስክረዋል፡፡
ይሁን እንጅ የዚያ ዘመን መርዝኛ አስተሰሰብ የዞረ ድምር ውጤት ዘመናትን ተሻግሮ ዛሬም ቢሆን ያ የቆረፈደ አመለካከት የተጣባቸው ግለሰቦች እና ቡድኖች አስተሳሰብ ምንጩ ሙሉ በሙሉ ደርቋል ለማለት ፍፁም አይቻልም፡፡ እነዚህ ግለሰቦች እና ቡድኖች ከባለፈው የቆሸሸ አገዛዝ የወረሱትን የዘረኝነት መርዝ በተለያየ መንገድ ሲያንፀባርቁ አሁንም ድረስ ይታያል፡፡ የእነዚህ ቡድኖች የዘረኝነት አመለካከት መገለጫዎች መካከል አንድን ብሔር ወይም ጎሳ በፈጣሪ አምሳል እንዳልተፈጠረ በማስመሰል የእነሱ የበታች በማድረግ ማንቋሸሽ፣ ሀይማኖት የለሽ ማስመሰል፣ በማንኛውም ነገር ሀሉ ኋላ ቀር አስመስሎ ማቅረብ፣ በተለያዩ ሚዲያዎች (በተለይ እነሱ በሚቆጣጠሩት ) እነሱ የአንድነት ሰባኪዎች ሌላው ደግሞ አገር አፍራሽ እንደሆነ መደስኮር፣ ገንጣይ አስገንጣይ እና የአገሪቱ ጠላትና ባንዳ አስመስሎ ማቅረብ፣ የራሳቸውን የዘር አመጣጥ በቅጡ ሳይውቁ እና ከየት እንደተገኙ ማስረዳት ሳይችሉ ሌላውን ህዝብ መጤ እና የአገሪቱ ባይተዋር ማድረግ፣ራሳቸውን መደበኛ ነዋሪዎች አስመስሎ ተራ ወሬ እና አሉባልታ ማስወራት፣ ታሪክ መሰል ሰው ሰራሽ ዲስኩር በየቤት እምነቱ መስበክ እና ትክክለኛ ለማስመሰል መሞከር፣ ፣ በአገሪቱ ውስጥ የተለያዩ የአስተዳደር፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ ተግዳሮቶች ሲከሰቱ ችግሩ የተከሰተው ሌሎች በአስተዳደር እርከኑ ከእነሱ ጋር መካተታቸውና እነሱ ከዳር አስከዳር አዛዥ እና ናዛዥ ባለመሆናቸው የመጣ አስመስሎ ችግሩን የሌለ ቀንድ እና ጅራት በመቀጠል ማራገብ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ለህዝብ የሚቀርብ የህትመትም ሆነ የኤሌክትሮኒክስ ዘገባ ከወግንተኝነት የፀዳ፣ በትክክለኛ መረጃ ላይ የተደገፈ፣ ለአንድ ወገን የማያደላ እና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በእኩልነት ሊያገለግል የሚችል መሆን ይገባዋል፡፡ የኢተዮጵያ ብሮድካሰቲንግ ህግ ለህዝብ የሚቀርብ ማንኛውም አይነት ህትመት አንድን ብሔር ከፍ ሌላውን ዝቅ በማድረግ መፃፍ፣ ህዝብን ከህዝብ ሊያጋጭ የሚችሉ ጹህፎችን ማውጣት በህግ የተከለከለ መሆኑን ያብራራል፡፡ ግን አንዳንድ ጋዜጠኛ ነን የሚሉ እና የሚዲያ አባላት ከዚህ በተቃራኒ ሲሰሩ ይታያል፡፡
ለዚህ ጹህፍ መነሻ የሆነኝ ‹‹ጋዜጠኛ›› ሙሉቀን ተስፋው በዋና አዘጋጅነት የሚያዘጋጃት ‹‹የቀለም ቀንድ›› የምትባል ጋዜጣ በተለያየ ጊዜ ይዛ የምትወጣው የተዛባ እና ለአንድ ወገን ብቻ ያደላ አስተሳሰብ እና መልዕክት ነው፡፡ ይህ ግለሰብ ምን ያክል ትከክለኛ የጋዜጠኝነት ሙያ እና ክህሎት ይኑረው አይኑረው በትክክል ባላውቅም በተደጋጋሚ በግል ጋዜጣው በሚለቀው የፁህፍ ይዘትን በመውሰድ ሙያው የጋዜጠኛ ሥነ-መግባር ያልተላበሰ መሆኑን በቀላሉ መገንዘብ ግን ይቻላል፡፡ የቀለም ቀንድ ዋና ዓላማ ትክክለኛ መረጃን ለህዝብ ማድረስ ሳይሆን ግለሰቡ በተደጋጋሚ የሚያነሳቸው ሀሳቦች አንድን ህዝብ ብቻ ለይቶ በወያኔ ዘረኝነት አስተዳደር በደል እንደደረሰበት፣ ከቦታው እንደተፈናቀለ፣ መሬቱ እንደተነጠቀ፣ በዘሩ ምክንያት የተለየ አስተዳደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ በደል እንደሚደርሰበት፣ እንደሚሞት አድርጎ ማውራት ነው፡፡ለዚህ የተዛባ እና ከጋዜጠኛ (ጋዜጠኛ ከሆነ ማለቴ ነው) ሥነ-መግባር የወጣ ዘገባ አብነት ይሆን ዘንድ ብዙ ነጎሮችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
የግለሰቡን የተዛባ እና የኮሰመነ አመለካከት ማየት የጀመርኩት ‹‹አዲስ ነገር›› በሚል ጋዜጣ ላይ አልፎ አልፎ ብቅ ሲያደርጋቸው በነበረው ዘረኛ፣ ቡድንተኛ እና ለአንድ መንደር ልጅ ያደላ መጣጥፎች ነበር፡፡ በመቀጠል መፃፍ አይሉት የስድብ ድርሳን በፃፈው መጽሀፍ የግለሰቡን ማንነት በግልፅ ቁልጭ አድርጌ ለማየት ችያለሁ፡፡ ግለሰቡ በፃፈው ‹‹የክፉ ሰው ሽንት›› በሚለው መጽሀፍ ውስጥ ባጨቀው ስደብ እና በመፅሀፉ ርዕስ ምከንያ ከ100 ገፅ በላይ ገፍቸ ማንበብ አላስቻለኝም፡፡ መፅፉን በመፅሀፍ መደርደሪያየ ዳግም እንዳላየው ፍጹም ስላልፈለኩ ለሸጠልኝ የመጽሀፍ ባለሱቅ የመጽሀፉን ዋጋ ሳልቀበለው መልሸዋለሁ፡፡
በመቀጠል የግለሰቡ የዘረኛነት እና የመንደርተኛነት ጥሙን ለማርካት ‹‹የቀለም ቀንደ›› (የነገር ቀንድ) የምትል ዘረኛ ጋዜጣ ማሳተም ቀጠለ፡፡ የጋዜጣው የዘገባ ይዘት በግለሰቡ የግል ግምገማ ‹‹ ተበደለ፣ ተፈናቀለ፣ በወያኔ ገልፅ እና ስውር ሴራ ማንነቱ ተሸረሸረ፣ የህዝብ ቁጥሩ ቀነሰ፣ ከሁሉም አቅጣጫ ተገፋ ለሚለው አንድ ህዝብ ብቻ ያደላ ነው፡፡
ይህ ግለሰብ ጋዜጣውን ማሳተም ከጀመረበት እለት ጀምሮ የግለሰቡ ጋዜጣ አጠቃላይ ማጠንጠኛ በአንድ እና በአንድ ነገር ብቻ ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መሬት ለሱዳን ተቆርሶ ተሰጠ፣ የሰሜን ጎንደር ለም መሬት በትግሬ ተወረረ፣ የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ የአማራ ማንነት በመጠየቁ ምክንያት በወያኔ መንግሥት መከራ እና ግፍ ደረሰበት፣ ወያኔ ጎንደርን ለመገነጣጠል ባለው ግልፅ ዓላማ ለዘመናት ጭቆናን እና መከራን አሜን ብሎ እና ሰጥ ለጥ ብሎ ሲገዛ ይኖር የነበረን የቅማንት ህዝብ በማነሳሳት የማንነት እና የራስ አስተዳደር ጥያቄ እንዲያነሱ በማድረግ አማራ እና ቅማንት እንዲጋጩ አደረገ፣ ወዘተ ከሚሉ ወጥቶ አያውቁም፡፡
የዚህ ግለሰብ የተዛባ አመለካከት መስተካከል ካልቻለ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ ጹህፎቹ ዉሎ አድሮ ዉጤታቸው የከፋ ይሆናል፡፡ በዚህ ግለሰብ አስተሳሰብ መሰረት እሱ ብቻ እና አሱ የመረጣቸው የኅብረተሰብ ከፍሎች ለኢትዮጵያ አንድነት ተቆርቋሪ ሌላው ግን ደንበር ቆርሶ ለጎረቤት አገር የሚያድል፣ እርሱ እና መሰሎቹ ለአገር አንድነት ተቆርቋሪ ሌላው ግን የኢትዮጵያ አንድነት ደንቀራ አስመስሎ የሚያይበት የተንሸዋረረ አመለካከት እጅግ ያሳዝናል፡፡ ማንም ኢትዮጵያዊ የኢትዮጵያን ስንዝር መሬት ለባዕድ ተቆርሶ እንዲሰጥ የማይፈቅድ መሆኑን እና አሁንም ድረስ በሱዳን ድንበር እነማን መስዋዕት እየሆኑ እንደሆኑ የሚያጣው አይመሰለኝም፡፡ ይህ ግለሰብ እና መሰሎች ይህን የውሸት አንድነት የሚሰብኩት ከሌላው ኢትየጵያዊ የተለየ የኢትጵያዊነት ደም ኑሮባቸው ሳይሆን ያ በቦታ አንድነት ስም በሌላው ህዝብ ላይ የሚያደርሱት መከራና ስቃይ ስለቀረ ብቻ የሚያደርጉት መንፈራገጥ ነው ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች በባለፈው ገዥዎች የመከራ አገዛዝ እንዴት እንደኖሩ የማንንም ምስክርነት አይሹም፡፡ በሥርዓቱ ምክንያት የተፈጠረው የመከራ ጠባሳ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጀርባ ላይ ስላለ ሁሉም ያውቁታል፡፡ ዛሬም በግልጽ ያን የዘረኝነት አስተሳሰብ በየመድረኩ የሚያቀረሹ ግለሰቦች እና የብአዴን ድርጅት አባላት እንዳሉ ማንም የሚክደው አይደለም፡፡ በባህር ዳር ከተማ ሰሞኑን ብአዴን በጠራው መድረክ መድረክ ለመናገር አይደለም ለማሰብ የሚያፀይፍ ንግግርን አድርገዋል፡፡ ቅማንት ወደ መጣበት ወደ ግብፅ ይመለስ የሚልና ሌላም የዘረኝነት ንግግር ተስተናግዷል፡፡ ይህን ፀያፍ ንግግር እንኳ ለማስተካከል የሞከረ የመድረክ አመራር አልነበረም፡፡
ሌላውን እና ዋነኛ የሆነው ግለሰቡ ሽምጥ የሚጋልብበት የዘረኝነት ፈረስ ሁሉም እንደሚያውቀው የቅማንት ህዝብ በተወለደበት ቀየው ተንቆ እና ተዋርዶ ለዘመናት የኖረ ህዝብ ለመሆኑ የዘረኝነትን መከራ የቀመሰ ህዝብ ሁሉ የሚዘነጋው አይመስለኝም፡፡ የቅማንት ህዝብ ለዘመናት በገዛ መሬቱ ለገዥዎች ገብሯል፣ በማንነቱ ተንቋል፣ ተንቋሻል፣ ተሰድቧል፣ ተዋርዷል፡፡ ገዥዎች እትብቱ በተቀበረበት መሬት ላይ መጤዎችን በማስፈር አስነጥቀውታል፤ በገዛ መሬቱ የገዥዎች እና የምስለኔዎች ገባር ሆኖ ለዘመናት አሳልፏል፡፡ ይህን ግፍ ይህ ግለሰብ እና የእሱ ቡድኖች በደንብ ያውቁታል፡፡
በአሀኑ ጊዜ በኢትዮጵያዊያን ቆራጥ ተጋድሎ እና ይሁንታ በፀደቀው ህገ-መንግሥት የኢትዮጵያ ህዝቦች የማንነት እና ራስን በራስ የማስተዳደር መብቶች ቢረጋገጡም የቅማንት ህዝብ ከባለፈው ሥርዓት የጭቆና እና የጨለማ አገዛዝ ናፋቂ ገዥዎች ሙሉ በሙሉ ሊላቀቅ ግን አልቻለም፡፡ ምክንያቱ ይህ ህዝብ የት እና በእነማን አገዛዝ ስር አሁንም ድረስ እንደሚኝ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በግልጽ ይረዳዋል፡፡ ዛሬም ቢሆን የቅማንት ህዝብ ከዚያ ከባለፈው ሥርዓት የዘረኝነት አስተሳሰብ አልተላቀቀም፡፡ ህገ-መንግሥቱን መሰረት በማድረግ እና በሰላማዊ መንገድ የቅማንት ህዝብ የጠየቀውን የማንነት እውቅና እና የራስ አስተዳደር ጥያቄ የተለያዩ ሚዲያዎች የቀለም ቀንድን ጋዜጣ ጨምሮ ‹‹የጎንደርን አንድነት ለማዳከም የተጠነሰሰ የወያኔ ድብቅ የመከፋፈል ሤራ›› በማለት እና የቅማንት ህዝብ የራሱን መብት የመጠየቅ መብት የሌለው ተደርጎ በመራገብ ላይ ይገኛል፡፡ ቅማንት በራሱ ምንም አይነት አቅም የሌለው ነገር ግን በወያኔ የዘረኝነት ሞተር የሚዘወር ግዑዝ ዕቃ አድርጎ በማሰብ ‹‹የወያኔ ባንዳ›› ተብሎም ስም ወጥቶለታል፡፡ እርግጥ ነው ህዝበ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ሀወሀት)ከሌሎች ነጻነት ወዳድ ህዝቦች እና ድርጅቶች ጋር በመሆን ህዝቦች በማንነታቸው እንዲኮሩ፣ በአካባቢያቸው ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ እና በማንነታቸው ምክንያት የአገዛዝ በደል እንዳይደርስባቸው በማድረግ ረገድ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ በተከፈለው የመስዋትነት ዋጋ ምክንያት ዛሬ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች የነፃነት አየር በመተንፈስ ላይ ይገኛሉ፡፡ የቅማነት ህዝብ የማንነት እና የራስ አስተዳደር ህገ-መንግሥታዊ ጥያቄም ቢሆን ምንጩና መሰረቱ የዚህ መስዋትነት ቱርፋት መሆኑ አይካድም፡፡ ይሁን እንጅ ህገ-መንግሥቱ ለኢትዮጵያ ህዝቦች በሙሉ ካጎናፀፈው እኩል መብት በተለየ ወያኔ ለቅማንት ህዝብ ምንም አይነት ውለታ አልዋለለትም፤ የቅማንት ህዝብ መብትም የሚመነጨው ከህገ-መንግሠቱ እንጅ ከአንድ የተለየ የፖለቲካ ድርጅት ወይም የግለሰቦች የድጋፍ እና ልዩ ስሜት አይደለም፡፡ የቅማንት ህዝብም ቢሆን ይህ ልዩ ድጋፍ እንዲደረግለት ፍፁም አይመኝም፤ አይፈልግምም፡፡ ህገ-መንግሥቱን መሰረት ያደረገ ሠላማዊ ትግሉን ግን በማንኛውም መንገድ ማንም አያቆመውም፤እስከመጨረሻው የሰዓት ሽርፍራፊ ድረስ ሰላማዊ ትግሉን ይቀጥልበታል፡፡
እጅግ የሚያሳዝነው የቅማንት ህዝብ ህገ-መንግሥታዊ የመብት ጥያቄ በማንሳቱ ምክንት ‹‹በአማራ ክልል ባለሥልጣን አመራር ሰጭነት የዘር ማጥፋት ጦርነት ታውጆበት በላይ አርማጭሆ ወረዳ፣ በጭልጋ፣ በመተማ እና በቋራ አራስ እናት ከእርጥብ ጫቅላዋ ጋር በክልሉ ልዩ ሀይል ፖሊስ ስትታረድ፣ የቅማንት ህዝብ ንብረት እና ቤቱ በገዛ ወገኑ(በልዩ ሀይል ፖሊስ እና ከየአቅጣጫው በክልሉ መንግሥት በተሰበሰቡ ወራሪ ቡድኖች) በእሳት እንዲጋይ ሲደረግ፣ የቅማንት ልጅ ቅማንት በመሆኑ ብቻ በመተማ ወረዳ በገንዳ ውኃ ከተማ ፣ በሽንፋ እንደበግ ሲታረድ፣ ገበሬው እና እረኛው በዋለበት እየታረደ ወደ ቤቱ ሳይመለስ ሲቀር፣ ከብቱ አንደጠላት ንብረት ሲዘረፍ እና ታርዶ ሲበላ፣ ለገበያ የመጡ ንፁኃን ሰዎች ደርግ በሀውዜን ህዝብ ላይ እንዳደረገው የግፍ ጭፍጨፋ በጭልጋ ወረዳ በአይከል ከተማ ሲረግፉ፣ የቅማንት እናት አምጣ የወለደችው እና ተቸግራ ያሰደገችው ልጇ በፊቷ ላይ እንደበግ ሲታረድ፣ የቅማንት ወጣቶች በገፍ በፍርደ-ገምድልነት ወደ እስር ቤት ሲወረወሩ እና ፍርድ አጥተው በእስር ለዓመታት ሲማቅቁ፣ የቅማንት ልጅ ቅማንት በመሆናቸው ብቻ በሚሰሩበት በአማራ ቀበሌዎች እየታደኑ ሲባረሩ፣ በየጊዜው በቅማንት ህዝብ ላይ የአማራ ልዩ ሀይል ፖሊስ ሽብርና የጅምላ ጭፍጨፋ ሲያደርግ የቀለም ቀንድ የምትባል ጋዜጣ የት ነበረች? በንፁሀን ህዝብ ላይ ሥለተፈፀመ መከራ እና ሰቆቃ ጋዜጣዋ ምን አለች? ጋዜጣዋ ከአድሎ ነፃ ለመሆኗ ማሳያ ስለሰው ልጅ የግፍ ዕልቂት ምን ነገር ዘገበች? አንድም ነገር አልተነፈሰችም፡፡
እጅግ የሚያሳፍረው በላይ አርማጭሆ ወረዳ በማውራ ቀበሌ እናት ከእነ ልጇ ስትታረድ፣ ሩጠው የማያመልጡ ሽማግሌዎችና እናቶች አልቃይዳ እንደፈጸመው የግፍ አገዳደል አንገታቸው በስለት እየተቀላ ሲገደሉ፣ የቀለም ቀንድ ምንም ነገር እንዳለየች ሆና አልፋለች፡፡ በቅማንት ህዝብ ላይ በተፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ምንም ነገር ላለማት የመረጠው የቀለም ቀንድ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በሳምንቱ በጎንደር ከተማ ማረሚያ ቤት በተነሳው የእሳት ቃጠሎ ‹‹47 ሰዎች ሞቱ›› ብሎ ዘገበ፡፡ ለምን ተዘገበ እያልኩ አይደለም፡፡ ከዚያ በፊት ግን በላይ አርማጭሆ ወረዳ በማውራ ቀበሌ በአማራ ፖሊስ ልዩ ሀይል ከመቶ በላይ የሚሆኑ ንፁህ የቅማንት ህዝብ በስለት ታርደው አና ተከትክተው በግፍ ተገለዋል፡፡ አራስ እናት ለመታረስ በተኛችበት አልጋዋ ላይ ከእንቦቀቅላ ጨቅላዋ ጋር በግፈኛ የፖሊስ ሀይሎች በግፍ ታርዳለች፡፡ ያኔ የቀለም ቀንድ የት ነበረች?
በመተማ እና በጭልጋ ወረዳዎች ብቻ ከ10 ሺ ህዝብ በላይ በግፈኞች እና በጦር ጠማኝ ወራሪዎች ከህዳር 29/2008 ጀምሮ ለአንድ ሳምንት የደረሰ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈፀምበት፣ ንብረቱ ሲወድም፣ የቀለም ቀንድ፣ ኢትየ-ምህዳር፣ አዲስ አድማስ የመሳሰሉ ወገኝተኛ ጋዜጦች ‹‹የቅማንት ህዝብ የአማራው ህዝብ ከጎንደር ይውጣልን በማለት ጦርነት ከፈተ›› የሚል ዘገባ ዘገቡ፡፡ እንደ ቪኦኤ የአማርኛው አገልግሎት እና ኢሳት እና የጎንደር ህብረት ተብየው የቦዘኔዎች ጥርቅም ድርጅት እና ዘረኛ ሚዲያዎች ደግሞ ጦርነቱ ‹‹ ወያኔ በሸረበው ሁለቱን ህዝቦች የማጋጨት ደባ በአማራ እና በቅማንት ብሔረሰብ መካከል የተፈፀመ አስመስሎ በመዘገብ የአማራን ክልል መንግሥት በቅማንት ህዝብ ላይ የፈፀመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ነፃ ለማድረግ በማሰብ ለሳምንታት ያክል አራገቡት፡፡ ሀቁ ግን ያ ጦርነት በክልሉ መንግሥት አማካኝነት በቅማንት ህዝብ ላይ የታወጀ እንጅ የሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች እንዳልነበር እነዚህ ሚዲያዎች ጭምር በደንብ ያውቁታል፡፡ ለዚህ ደግሞ በመተማ፣ በቋራ እና በጭልጋ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች በግልፅ ስለተፈፀመው ሁሉ ተናግረዋል፡፡ ከፌደራል መንግሥት ለሄዱ ባለሥልጣናት ‹‹እናንተ የአማራ ክልል የመንግሥት አመራሮች ወንድም የሆኑት ሁለቱ ወገን እንዲጋጭ አመራር ከሰጣችሁን በኋላ አስታራቂ መስላችሁ መምጣታችሁ ገርሞናል›› ነበር ያሉት፡፡ የቅማንት ህዝብም ቢሆን ወገን የሆነው የአማራ ህዝብ ምንም አንዳላደረገው እና ጥቃት የተፈፀመበት የክልሉ መንግሥት ባሰመራቸው የክልሉ ፖሊስ እና ወንበዴ ቡድኖች መሆኑን በግልፅ ለሚመለከተው አካል አስረድቷል፡፡
በአንድ ሳምንት ልዩነት በኦሮሚያ ክልል በአመያ ወረዳ በዘር ጥላቻ በመነሳሳት በአማርኛ ተናጋሪ ህዝቦች የደረሰን መፈናቀል፣ የንብረት ውድመት እና በጥቂት ግለሰቦች ላይ የተቃጣ ጥቃትን የቀለም ቀንድ የምትባል ጋዜጣ ‹‹ አመያ ሶዶም ወ ጋሞራ›› በሚል ርዕስ በልዩ ዘገባ በጋዜጣው ላይ በመዘገብ ህዝብ እንዲያውቀው ስታደርግ በተቃራኒው በመተማ እና በጭልጋ ወረዳዎች በክልሉ መንግሥት አመራር ሰጭነት እና አስተባባሪነት ህዳር 29/2008 ዓ.ም ጀምሮ በተከታታይ በተፈፀመው የዘር ማጥፋት ዘመቻ ብቻ አስካሁን ድረስ ከ150 በላይ ሰዎች ህይወታቸው አልፏል፣ ከ50 በላይ የደረሱበት አይታወቅም ከ100 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆን ንብረት ወድሟል፡፡ ሰለዚህ ጉዳይ ግን የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ምንም ማለት አልፈለገም፡፡
እጅግ ያሳዘነኝ እና መቋጫ የሌለው የአቶ ሙሉቀን ዘረኝነት ዘገባ መጋቢት 20/2008 ዓ.ም ባወጣው የግል ጋዜጣው ላይ ‹‹ከጎንደር አስከ አርማጭሆ- የግጨው ግጭትትና የኢትዮ- ሱዳን ድንበር (ክፍል 3)››በሚል ርእስ ባወጣው ጋዜጣ የዘረኛ መርዙን ዳግም በቅማንት ህዝብ ላይ አራግፏል፡፡
በዚህ ዘገባው ላይ ‹‹ቅማንቶች ዘረኝነት የተጠናወታቸው በመሆናቸው ለዘመናት በሰላም የተገነባን ትዳር በማፍረስ አማራ ባል ወይም ሚስት እንዲኖረኝ አልፈልግም በማለት የቅማንት ሚሰት ለአማራ ባሏ እርጥብ ጫቅላዋን አሳቅፋው ወደዘመዶቿ ሰፈር ኮበለለች›› በማለት ይነግረንና በተቃራኒው ግን የእሱ ወገን የሆነው ሚስቱ ትታው የሄደችው ባል የሚያውቀው ቢኖር ሚስቱ ሰው መሆኗን ብቻ እንጅ ዘሯ ምን ይሁን ምን ትታው እስከሄደችበት ጊዜ ድረስ እንደማያውቅ ሊነገረን ይሞክራል፡፡ ‹‹ ለማያውቅሽ ታጠቢ!›› ማለት ይህኔ ነው፡፡ እውነቱ ግን ዋና አዘጋጁ እንዳለው ሳይሆን የቅማንት ሴት ወይም ወንድ ቅማንት መሆኗ(ኑ)ን በደንብ የሚያውቀው በትዳር አጋሩና በባል ወይም በሚስት ቤተሰቦች ወይም ደግሞ በራሱ ጓደኞቹ እና ጎረቤቱ በሚደርሰባቸው የዘረኝነት የስድብ ናዳ ነው፡፡ ቅማንቶች ሰውን ሰው ከመሆን ያለፈ አጥንት ቆጠራ እንደማያደርጉ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ጭምር የሚያውቅ ይመስለኛል፡፡ ይሁን እንጅ በቅማንት ህዝብ ላይ ያለውን ጥላቻ ለማሳየት ሲል ‹‹ጋዜጠኛው›› ራሱን ቅዱስ ቅማንትን ደግሞ ዘረኛ ለማድረግ ሞከረ፡፡ እውነቱ ግን የተገላቢጦሽ ለመሆኑ ድፍን ጎንደር እና ግለሰቡ የተገኘበት በጌምድር ይህን ጉዳይ በደንብ ያውቀዋል፡፡
ይህ ግለሰብ ጥላቻው በቅማንት ህዝብ ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ አራምባ እና ቆቦ በሚረግጠው ዘገባው ወደ አርማጭሆ ሲሄድ አልፎ በሚሄድበት በሰሜን አቅጣጫ ጎንደር መግቢያ የሚገኝ ሙሽራ ድንጋይ ተብሎ በሚጠራ ቦታ አካባቢ ሲደረስ ሌላ የዘረኝነት ዛር ተሳፈረበት፡፡ ህዝቦች ያለፉት ዘረኛ ገዥዎች የሚያደረሱባቸውን ግፍ አቤቱታ ዙረው ለእነሱ ለማቅረብ ገዥዎች ወደሚገኙበት ከተማ ሲመጡ እንደ አንድ ዜጋ በቀጥታ ወደ ጎንደር ከተማ መግባት አይችሉም ነበር፡፡ መምጣቸውን ለገዥዎች አና ለገዥዎች አሽከሮች ለማሳወቅ ጎንደር መግቢያ ላይ የሚገኘ አንድ ከፍታ ቦታ ላይ በመሆን ጮክ ብለው ያሰማሉ፡፡ ገዥዎች ፈቃደኛ ከሆኑ ወደ ከተማው ገብተው እና ወደ ገዝዎች ቀርበው የደረሰባቸውን በደል ያሰማሉ፡፡ የአንድ አገር ዜጋ ሆኖ በገዛ አገሩ ከተማ በነፃ ገብቶ በደሉን እንዳያሰማ ይደረጉ ከነበሩት ዜጎች መካከል ትግርኛ ተናጋሪው ህዝብ አንደኛው ነበር፡፡ ይህን ለአቤቱታ መምጣታቸውን ያሰሙበት የነበረውን ቦታ ገዥዎች እና የገዥ አሽቃባቾች አስካሁን ድረስ ‹‹ትግሬ መጮኸያ›› ብለው ይጠሩታል፡፡ ይህ ድርጊት በዚያ ዘመን በቅማንቶች ዘንድ ከደረሰው የዘረኝነት (አፓርታይድ) ጋር ሲነፃፀር እጅግ ኢምንት ይመስለኛል፡፡ ከዚህ የሚብሰው የቅማንት ህዝብ የእርሻ ምርቱን ጎንደር ከተማ ገብቶ እንዳይሸጥና በከተማ የሚገኙ ሸቀጦችን ወደ ጎንደር ከተማ ገብቶ እንዳይገዛ ‹‹ጋዜጠኛ›› ሙሉቀን ትግሬ መጮኽያ ብሎ ከጠራው አካባቢ አልፎ እንዳይገባ ይከለከል ነበር፡፡ይዞ የመጣወን የእርሻ ምርትም ከዚያው ሽጦ እንዲመለስ ይደረግ እንደነበር ዋና አዘጋጅ ሙሉቀን አያውቅ ይሆን? ይህ ግለብ እና መሰሎቹ ‹‹ደጉ ዘመን እና የአንድነት ተምሳሌት›› ብለው የሚዘመሩለት ያ የግፍ የአገዛዝ ዘመን ይህን ይመስል ነበር፡፡ አፓርታይድ፣ የዘር ማጥፋት ወንጀል በጎንደር መሬት ተፈፅሟል፡፡ ሰሜነኞች (የአገው ዘር ክፋይ የሆኑት) በገዛ አገራቸው ፈላሻ ተብለው ከእርስት ተነቅው በመጨረሻ ኢትዮጵያን ጥለው ወደ ማያዉቁት አገር አንዲሰደዱ ተደርገዋል፡፡ ሸክላ እና ብረት ቀጥቅጠው መኖር የቻሉት በቅማንቶች አካባቢ በመጠለል ነበር፡፡
ሌላው ይህ ለቅማንት ህዝብ ያለውን ጥላቻ ለመግለፅ ከጎንደር አስከ አርማጭሆ የሚለውን ሪፖርታዥ ለመስራት ከጎንደር ተነስቶ በላይ አርማጭሆ ወረዳ ከተማ (ትክልድንጋይን) ረግጦ ሲሄድ እና ሳንጃ ከተማ ሲደርስ ትናት የተመሰረተችው የሳንጃ ከተማ አዝጋሚ የእድገት ሂደት ሲያንገበግበው ከ70 ዓመት ያላነሰ ዕድሜ ያስቆጠረችው ትክልድንጋይ ከተማ የእድገቷ መቀጨጭ እና ጉስቁልናዋ ትንሽም ሊመለከትላት እልፈለገም፡፡ ትክልድንጋይ ከተማ ረግጦ ሲያፍ እሱ ሊያስታውስ የፈለገው ነገር ቢኖር በቅማንት የማንነት ጥያቄ ምክንት አካባቢው የስጋት ቀጠና መሆኑን ብቻ ነው፡፡
ይህ ግለሰብ እውን ትክክለኛ ጋዜጠኛ ከሆነ ህገ-መንግሥታዊ የመብት ጥያቄ በማንሳታቸው ምክንያት በአሁኑ ሰዓት ያለፍርድ የጎንደር አስር ቤቶችን ስለሞሉት እና በግፍ ስለሚማቅቁ የቅማንት ልጆች ለምን መፃፍ ተፀየፈ? መጋቢት 16/07/2007 በላይ አርማጭሆ ወረዳ በትክል ድንጋይ ከተማ በአማራ ክልል ልዩ ሀይል በግፍ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ስለተገደሉ ግለሰቦች እና የሽብር ድርጊትት ለምን ትንሽ ማለት አልፈለገም? ይህ የግፍ ድርጊት ግለሰቡ ‹ወገኔ› በሚለው ህዝብ ላይ ቢፈፀም ኑሮ የጋዜጣው ርዕስ አንቀፅ ‹ ሶዶም ወ ጋሞራ› ይሆን ነበር፡፡ ግን ይህ ድርጊት የተፈፀመው በቅማንት ህዝብ ሆነና ዝምታን መረጠ፡፡
እንዲህ አይነት ሰዎች ናቸው ከድሮ አስከአሁን በተጨፈነ የዘር ጥላቻ ተሞልተው ስለባዶ የአገር አንድነት ሲሰብኩ የሚደመጡት፡፡ የሌላው ወገን ህዝብ ሞት እና ስቃይ እንግልት እና መከራ ምንም ሳይመስለው እነሱ የእኔ በሚሉት ህዝብ ላይ ትንሽ ነገር ሲደርስ ላንቃቸው እስኪሰነጠቅ መጮህ ከዘረኝነት ያለፈ ሌላ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም፡፡
ሥለሰው ልጆች እንቆረቆራለን የሚል ሰብአዊ ድርጅቶች እና መረጃን ለህዝብ እናደርሳለን ብለው በህግ የተቋቋሙ የህትመት እና በሮድካስቲግ ተቆማት መረጃውን ከማስተላለፋቸው በፊት እነሱ ከዘረኝት አስተሳሰባቸው ሊፈወሱ የግድ ይላል፡፡ በታመመ የዘረኝነት ጭንቅላት ስለአገር አንድነት መስበክ አይቻልም፡፡ የእነሱ የተዛባ አስተሳሰብ ሳይሰተሰተካከል ስለአገር አንድነት የመሰበክ ሞራሉ ሊኖራቸው አይችልም፡፡
ከቆሻሻ ቅመም የተዘጋጀ ሳሙና እድፍን እንደማያስለቅቅ ሁሉ ዘረኛ አስተሳሰብ የተጠናወተው ግለሰብ ስለአንድነት ፍጹም ሊሰብክ አይችልም፡፡

Advertisements
This entry was posted in Agaw Kemant. Bookmark the permalink.

One Response to Soap made from Dirt Can’t Remove Dirt: Are You Journalist or Racist?

  1. Chalew says:

    በጣም ታሳዝናላችሁ! ተስማምቶ የሚኖረውን ህዝብ ከዚህ ሁሉ ያደረሳችሁ ማንም አይደለም እናንተው ናችሁ። አሁን ደግሞ ህሊና እንዳለው ሰው ይህን ሁሉ ስትቀባጥሩ አታፍሩም።
    እኔ በሁኔታው ያዘንኩ የቅማንት ልጅ ነኝ። ሌላ አልልም እግዜኢብሄር ልብ ይስጣችሁ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s