የፌዴራል መንግስት የቅማንትን ጉዳይ ለመፍታት ጣልቃ የሚገባበት የህግ ስርዓት (Legal Framework Federal Government to Intervene on Kemant Issue)

By Tilahun Jember
1. ስለጣልቃ ገብነት በጥቅሉ

1.1. መግቢያ
የፌዴራሉ ህገ-መንግስት አንቀፅ 1 የሚከተለዉን ደንግጓል፤
“ይህ ህገ-መንግስት ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ የመንግስት አወቃቀር ይደነግጋል፡፡ በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በሚል ስም ይጠራል፡፡”
ከዚህ የህገ-መንግስት ድንጋጌ መገንዘብ እንደምንችለዉ የፌዴራሊዝም እና የዴሞክራሲ ስርዓት መርሆች የመንግስታችን አወቃቀር ምሰሶዎች መሆናቸዉን ነዉ፡፡ ከዚህ አንፃር የፌዴራል መንግስቱ አባል የክልል መንግስቶች ስም ዝርዝር እና ሌሎች ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች የራሳቸዉን ክልላዊ መንግስታት የሚያቋቁሙባቸዉን ስርዓት የፌዴራሉ ህገ-መንግስታችን በአንቀፅ 47 ስር በሚገባ አስቀምጧል፡፡ የፌዴራሊዝም ስርዓት ለፌዴራል መንግስቱና ለክልል መንግስታት የማስተዳደር ስልጣን አከፋፍሎ የሚሰጥበት ስርዓት እንደመሆኑ መጠን በአገራችንም የፌዴራል መንግስትና የክልል መንግስታት የአስተዳደር ስልጣን የሚከፋፈሉበት የህግ ስርዓት ተዘርግቷል (የፌዴራል ህገ-መንግስት፣ አንቀፅ 50-52)፡፡ የፌዴራል መንግስቱ ስልጣኖችና ተግባሮች በፌዴራሉ ህገ-መንግስት አንቀፅ 51 ስር ተዘርዝረዉ የተቀመጡ ሲሆን የክልል መንግስታት ስልጣን እና ተግባሮች ደግሞ በአንቀፅ 53 ስር ተቀምጠዋል፡፡ በፌዴራል መንግስቱና የክልል መንግስታት መካከል የሚኖረዉን የስልጣን ግንኙነት በሚመለከት የፌዴራል ህገ-መንግስቱ አንቀፅ 50(8) በሚከተለዉ አግባብ ደንግጎታል፤
“የፌዴራሉ መንግስትና የክልሎች ስልጣን በዚህ ህገ-መንግስት ተወስኗል፡፡ ለፌዴራሉ መንግስት የተሰጠዉ ስልጣን በክልሎች መከበር አለበት፡፡ ለክልሎች የተሰጠዉ ስልጣን በፌዴራሉ መንግስት መከበር አለበት፡፡”
ስለሆነም የፌዴራሉ መንግስትና ክልሎች የፌዴራሉ ህገ-መንግስት በግልፅ ከሚያስቀምጠዉ ዉጭ አንዱ ባንዱ ጉዳይ እንደፈለገ ጣልቃ የሚገባበት ህጋዊ ስርዓት እንደሌለ መረዳት አያዳግትም፡፡
የክልል መንግስታት በፌዴራሉ ህገ-መንግስት በግልፅ ከተሰጣቸዉ ስልጣንና ተግባሮች መካከል፡-
 ራስን በራስ ማስተዳደርን ዓላማ ያደረገ ክልላዊ መስተዳድር ማዋቀር፣
 የህግ የበላይነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት፣
 የፌዴራሉን ህገ-መንግስት መጠበቅና መከላከል፣
 የክልሉን የፖሊስ ኃይል ማደራጀትና መምራት እና
 የክልሉን ሰላምና ፀጥታ ማስጠበቅ የሚሉት ይገኙበታል፡፡
የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት (አብክመ) የፌዴራል መንግስቱን ካቋቋሙት አባል የክልል መንግስቶች መካከል አንዱ የክልል መንግስታችን መሆኑንም እንገነዘባለን፡፡
1.2. የአዋጅ ቁጥር 359/1993 አንድምታ
የፌዴራል መንግስት በክልሎች ጉዳይ ጣልቃ የሚገባዉ መቼ ነዉ? ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ከመሞከራችን በፊት ባንድ ወቅት የቀድሞዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ በዚህ ጉዳይ ላይ ተጠይቀዉ ምላሽ የሰጡትን እንመልከት፡፡ የቀረበላቸዉ ጥያቄም የሚከተለዉ ሲሆን “የፌዴራል መንግስት በክልሎች ጉዳይ ጣልቃ መግባቱ የፌዴራል ስርዓቱን አይሸረሽርም?” ምላሽቸዉም የሚከተለዉን ይመስላል፤
“ህገ-መንግስቱ የፌዴራል መንግስት በክልሎች ጉዳይ ጣልቃ ስለሚገባበት ሁኔታ መሰረታዊ መርሆችን የሚያካትቱ ሶስት አንቀፆችን አካቷል፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያወጣዉ የነዚህን አንፆች ማስፈፀሚያ አዋጅ ነዉ፡፡ በህገ-መንግስቱ ዉስጥ የፌዴራል መንግስት በክልሎች ጉዳይ ጣልቃ ስለሚገባበት ሁኔታ የተቀመጡትን መርሆች እንዴት እናስፈፅም በሚለዉ ጥያቄ ላይ ቀደም ሲል ኢህአዴግ በሁለቱም ቦታዎች፣ ማለትም በክልሎችና በፌዴራል መንግስት ዉስጥ ስላለ፣ በመግባባት ሲፈፀም ነበር የቆየዉ፡፡ ይህ አሰራር ተገቢ አይደለም፤ በህግ መደንገግ አለበት፡፡ ስለዚህ ህገ-መንግስቱን ለማስፈፀም የወጣ አዋጅ እንጅ ህገ-መንግስቱን ለማሻሻል ወይም ለመቀየር አይደለም፡፡ ህገ-መንግስቱ ዉስጥ በግልፅ የተደነገገዉ ፌዴራል መንግስቱ በዚህ፣ በዚህ ምክኒያት በክልሎች ጉዳይ ጣልቃ ሊገባ ይችላል የሚል ነዉ፡፡ በመሆኑም ህገ-መንግስቱ ላይ የተቀመጠዉን ነገር ለማስፈፀም የሚያስችል ህግ ነዉ ያወጣነዉ፡፡ በነገራችን ላይ ፌዴራል መንግስት በክልሎች ጉዳይ ጣልቃ የሚገባበትን ሁኔታ በህግ ለይቶ ያላስቀመጠ የፌዴራል ስርዓት በዓለም የለም፡፡ ይሄም በመሆኑ ነዉ ህገ-መንግስታችን ራሱ የፌዴራል መንግስት በክልሎች ጣልቃ የሚገባባቸዉን በጣም ዉስንና ግልፅ መርሆዎች ያስቀመጠዉ፡፡ ይህን ለማስፈፀም የሚችል የአፈፃፀም አዋጅ ብቻ ነዉ ያወጣነዉ፡፡ የፌዴራሊዝም ስርዓቱ በምንም ዓይነት መልኩ የሚነካ አይደለም፤መነካትም የለበትም፡፡ ለአገራችን የሚበጀዉ ስርዓት እሱ ነዉ፡፡ ለዘለቄታዉም የሚያስኬደን መንገድ እሱ ነዉ…ኢህአዴግ የፌዴራል ስርዓቱን የመሸራረፍ ሃሳብ ለአንዲት ሴኮንድ እንኳን ማስተናገድ አይፈቀድም፡፡” (‘መለስ፣ ከልጅነት እስከ እዉቀት’ ከሚለዉ መፅሐፍ ገጽ 77-78 የተወሰደ)
የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሀሳብና የፌዴራሉ ህገ-መንግስታችን በክልሎች ጣልቃ ስለሚገባበት ስርዓት ያላቸዉ አቋም ተመሳሳይ ነዉ፡፡ የፌዴራል መንግስቱ በክልሎች ጣልቃ ሊገባባቸዉ የሚችልባቸዉን ሁኔታዎች ህገ-መንግስቱ በግልፅ እንደሚከተለዉ አስቀምጧል፤
1) በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 51(1) መሠረት ፌዴራል መንግስቱ ህገ-መንግስቱን የመጠበቅና የመከላከል ስልጣንና ኃላፊነት ተሰጥቶታል፣
2) በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 51(14) ከክልል አቅም በላይ የሆነ የፀጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም በክልሉ መስተዳድር ጥያቄ መሠረት የፌዴራል መንግስቱ የመከላከያ ኃይል እንደሚያሰማራ ተደንግጓል፣
3) በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 55(16) በማናቸዉም ክልል ሰብአዊ መብቶች ሲጣሱና ክልሉ ድርጊቱን ማቆም ሳይችል ሲቀር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በራሱ አነሳሽነት እና ያለክልሉ ፈቃድ ተገቢዉ እርምጃ እንዲወሰድ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እና ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ ጥያቄ በማቅረብ በተደረሰበት ዉሳኔ መሠረት ለክልሉ ምክር ቤት መመሪያ እንደሚሰጥ ተደንግጓል፣
4) በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 62(9) ማናቸዉም ክልል ህገ-መንግስቱን በመጣስ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ፌዴራል መንግስቱ ጣልቃ እንዲገባ እንደሚያዝ ተደንግጓል፡፡
አዋጅ ቁጥር 359/1993 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጣበት ምክኒያትም ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን የህገ-መንግስቱን ድንጋጌዎች ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ህጋዊ ስርዓት ለመዘርጋት መሆኑን ለመረዳት አያዳግትም፡፡ በዚህ መንፈስ የአዋጁን ዋና ዋና ድንጋጌዎች አንድ ባንድ በሚከተለዉ አግባብ ለማየት እንሞክራለን፡፡
1.2.1. በፀጥታ መደፍረስ ምክኒያት ስለሚደረግ ጣልቃ ገብነት
በአንድ ክልል ዉስጥ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት የሚያዉክ እንቅስቃሴ ሲደረግና የተፈጠረዉን የፀጥታ ችግር የክልሉ ህግ አስከባሪ እና የዳኝነት አካል በህጋዊ መንገድ ለመፍታት የማይችሉበት ሁኔታ ሲፈጠር የፀጥታ መደፍረስ እንደተፈፀመ ይቆጠራል (አዋጅ ቁጥር 359/1993፣ አንቀፅ 3)፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ማናቸዉም ክልል በራሱ ኃይል ሊቋቋመዉ የማይችለዉ የፀጥታ መደፍረስ ያጋጠመዉ እንደሆነ የክልሉ ምክር ቤት ወይም የክልሉ ከፍተኛ የህግ አስፈፃሚ አካል በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በኩል ጥያቄዉን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚያቀርብ ተደንግጓል (አዋጅ ቁጥር 359/1993፣ አንቀፅ 4)፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፀጥታዉን መደፍረስ ለመቆጣጠር እንደ ችግሩ ክብደት የፌዴራል ፖሊስ ወይም የመከላከያ ሠራዊት ኃይልን ወይም ሁለቱንም ያሠማራል፤ የሚሰማራዉ ኃይል በሚመለከተዉ የፌዴራል መንግስት አካል የሚታዘዝ ይሆናል (አዋጅ ቁጥር 359/1993፣ አንቀፅ 5(1))፡፡ የሚሰማራዉ ኃይልና በኃይሉ የሚወሰደዉ እርምጃ የፀጥታዉን መደፍረስ ለመቆጣጠርና ህግና ስርዓት ለማስከበር የሚያስችል ተመጣጣኝ ኃይል ወይም እርምጃ መሆን ይኖርበታል (አዋጅ ቁጥር 359/1993፣ አንቀፅ 5(2))፡፡ የክልሉ መንግስት የፀጥታዉን መደፍረስ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ መረጃዎችን የመስጠት እና ሁኔታዎችን የማመቻቸት ኃላፊነት ይኖርበታል (አዋጅ ቁጥር 359/1993፣ አንቀፅ 5(3))፡፡ የሚሰማራዉ ኃይል በፀጥታዉ መደፍረስ የተሳተፉ ሰዎችን ለፍርድ ለማቅረብ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሚገባዉ ተደንግጓል (አዋጅ ቁጥር 359/1993፣ አንቀፅ 5(4))፡፡ የፀጥታዉ መደፍረስ በቁጥጥር ስር ከዋለ ወይም የክልሉ ከፍተኛ የህግ አስፈፃሚ አካል ወይም የክልሉ ምክር ቤት የተሠማራዉ ኃይል ተልዕኮ እንዲያበቃ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ካቀረበ የተሰማራዉ ኃይል ተልዕኮዉ እንደሚያበቃ በግልፅ ተቀምጧል (አዋጅ ቁጥር 359/1993፣ አንቀፅ 5(5))፡፡

1.2.2. በሰብአዊ መብት መጣስ ምክኒያት ስለሚደረግ ጣልቃ ገብነት
በአንድ ክልል ዉስጥ በህገ-መንግስቱና ህገ-መንግስቱን መሠረት አድርገዉ በወጡ ህጎች የተመላከቱትን የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች የመጣስ ድርጊት ሲፈፀምና በህግ አስከባሪዉ እና በዳኝነት አካሉ በቁጥጥር ስር ለማዋል ካልተቻለ የሰብአዊ መብት መጣስ ድርጊት እንደተፈፀመ ይቆጠራል (አዋጅ ቁጥር 359/1993፣ አንቀፅ 7)፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማናቸዉም ክልል ዉስጥ የፌዴራል መንግስቱን ጣልቃ ገብነት የሚጠይቅ የሰብአዊ መብት የመጣስ ድርጊት መፈፀሙንና ክልሉ ድርጊቱን ማቆም አለመቻሉ ከሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ የሰብአዊ መብት መጣስ ድርጊት ከተፈፀመበት ክልል ተወካዮች ወይም ከሌላ ከማናቸዉም ሰዉ መረጃ ሲደርሰዉ ጉዳዩን የሚያጣራ ቡድን ወደ ክልሉ ሊልክ እንደሚችልና ቡድኑ ከተወካዮች ምክር ቤት የተዉጣጡ አባላትን የያዘ እንደሚሆን በግልፅ ተቀምጧል (አዋጅ ቁጥር 359/1993፣ አንቀፅ 8(1))፡፡ አጣሪ ቡድኑ ይዞት የቀረበዉ ሪፖርት ተቀባይነት ካገኘ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጋር በሚያደርጉት የጋራ ስብሰባ ዉሳኔ መሠረት ክልሉ የሰብአዊ መብት መጣስ ድርጊቱን እንዲያቆም፣ ሰብአዊ መብት የጣሱትን ሰዎች ለፍርድ እንዲያቀርቡና ሌሎች አግባብነት ያላቸዉን እርምጃዎች እንዲወስዱ መመሪያ እንደሚሰጥ ተደንግጓል (አዋጅ ቁጥር 359/1993፣ አንቀፅ 11)፡፡

1.2.3. ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ አደጋ ላይ በመዉደቁ የሚደረግ ጣልቃ ገብነት
በአንድ የክልል መንግስት ተሳትፎ ወይም ዕዉቅና ህገ-መንግስቱን ወይም ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ባለማክበር የሚደረግ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት በተለይም፤
1) በትጥቅ የተደገፈ የአመፅ እንቅስቃሴ ማድረግ፣
2) ከሌላ ክልል ወይም ከሌላ ብሄር፣ብሄረሰብ ወይም ህዝብ ጋር የተፈጠሩ ችግሮችን ሰላማዊ ባልሆነ መንገድ መፍታት፣
3) የፌዴራሉን ሰላምና ፀጥታ ማናጋት ወይም
4) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአንድ ክልል ዉስጥ የተፈፀመዉን የሰብአዊ መብት ጥሰት አስመልክቶ የሰጠዉን መመሪያ አለማክበር ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት እንደሆነ ይቆጠራል (አዋጅ ቁጥር 359/1993፣ አንቀፅ 12)፡፡
በዚህ መንገድ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በማንኛዉም ክልል ዉስጥ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት መፈፀሙን ካረጋገጠ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የጣለዉን ሁኔታ ለማስወገድ የሚያስችሉ ስር-ነቀል እርምጃዎች ማለትም ለፌዴራል መንግስቱ ተጠሪ የሆነ ጊዜአዊ አስተዳደር እስከማቋቋም ድረስ ሊሄድ እንደሚችል በግልፅ ቋንቋ ተቀምጧል (አዋጅ ቁጥር 359/1993፣ አንቀፅ 15)፡፡ የፌዴራል መንግስቱ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ በመጣል የተሳተፉ የክልሉ መንግስት ባለስልጣኖች፣ ተሿሚዎች፣ ተመራጮች፣ የፖሊስና የፀጥታ ኃይል አባላት እና ሌሎች ሰዎችን ለፍርድ እንዲቀርቡ የማድረግ እንዲሁም በክልሉ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ ተጠብቆ የክልሉ መንግስት መደበኛ ስራዉን የሚጀምርበትን ሁኔታ በአፋጣኝ የማመቻቸት ኃላፊነት እንዳለበት አዋጁ ደንግጓል (አዋጅ ቁጥር 359/1993፣ አንቀፅ 14(3))፡፡

2. የፌዴራል መንግስት የቅማንትን ጉዳይ ለመፍታት ጣልቃ የሚገባበት አግባብ
በጥቅሉ የፌዴራል መንግስት በክልል ጉዳዮች ጣልቃ የሚገባባቸዉን ህጋዊ መንገዶች ለማዬት ሞክረናል፡፡ የቅማንት ብሄረሰብ የራስ አስተዳደር በ42 ቀበሌዎች ብቻ መቋቋም ይገባዋል የሚለዉ የክልላችን መንግስት ዉሳኔ በተግባር የህዝብ ተቃዉሞ ገጥሞታል፡፡ ይህንን ህዝባዊ ተቃዉሞ ተከትሎም የክልላችን መንግስት የህዝቡን ፍላጎት ያማከለ ዉሳኔ ለመወሰን ትክክለኛ እርምጃ መዉሰድ ሲገባዉ ወይም ደግሞ ተቃዉሞዉን በሠላማዊና በሰለጠነ አኳኋን መፍታት እየተገባ ከሰኔ 06 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ በኃይል በጠመንጃ ጉዳዩን ለመፍታት መሞከሩ በእዉነቱ አስተባባሪ ኮሚቴዉንም የህዝቡን ጥያቄ በዉክልና ይዞ ባግባቡና በሠላማዊ መንገድ ለመምራት በእጅጉ የተፈታተነ ጉዳይ መሆኑ የሚታወቅ ነዉ፡፡ የቅማንት ህዝብም ከክልላችን መንግስት ፀጥታ አስከባሪዎች ጋር በሚደረጉ አላስፈላጊ ግጭቶች ሳቢያ ጉዳዩን ለማስቆም ከክልሉ መንግስት አቅም በላይ በመሆኑ የፌዴራል መንግስት ሠላም አስከባሪ ኃይል የቅማንት ህዝብ በሰፈረበት አካባቢ ጣልቃ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ ከሰኔ 06 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ የክልላችን መንግስት በፈጠረዉ የመልካም አስተዳደር ችግር ምክኒያት በቅማንት ተወላጆች ላይ አይን ያወጣ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተካሂደዋል፡፡ ከክልሉ ፀጥታ አስከባሪ ልዩ ኃይል ጋር በተፈጠረዉ አላስፈላጊ ግጭት ወይም ጦርነት ሳቢያም በርካታ ህይወት ጠፍቷል፡፡ አሁንም ቢሆን ፀረ-ሠላም ኃይሎች የግል ፍላጎታቸዉን ለማሳካት በማሰብ የቅማንትን ህገ-መንግስታዊ ጥያቄ ሽፋን አድርገዉ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ በሚጥል ሁኔታ ለዘመናት ተቻችለዉ በጉርብትና የሚኖሩትን ወንድማማች የቅማንትና አማራ ህዝቦችን አጋጭተዉ ደም አቃብተዋል፤ ዘግናኝ የሆኑ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተፈፅመዋል፡፡ የእነዚህን ጥፋቶች መሠረታዊ መንስኤ ስንመለከት ደግሞ በክልላችን መንግስት በኩል የቅማንትን የራስ አስተዳደር በ42 ቀበሌዎች ብቻ በኃይልና በጉልበት ለማቋቋም ሙከራ መደረጉ ነዉ፡፡
ይህ ሁሉ ባለበት ሁኔታ የፌዴራል መንግስት ጣልቃ ገብቶ የቅማንትን የራስ አስተዳደር አከላለል በሚመለከት በህዝብ ፍላጎት ላይ ተመስርቶ በዘላቂነት ችግሩን መፍታት ካልተቻለ ህገ-መንግስታዊ ስርዓታችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ ዝንባሌዎችና እንቅስቃሴዎች በተጨባጭ እየታዩ ናቸዉ፡፡ ከዚህ በላይ በተጠቀሱት የህግ ድንጋጌዎች የፌዴራል መንግስታችን በክልላችን መንግስት ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ የቅማንትን የራስ አስተዳደር ጥያቄ ዘላቂ መፍትሄ የማይሰጥበት አግባብ ምንድነዉ? ስለሆነም በአጠቃላይ የፌዴራል መንግስት የቅማንትን ጉዳይ ለመፍታት በክልላችን መንግስት ጣልቃ የሚገባበት አግባብ የለም የሚለዉ የፀረ-ሠላም ኃይሎች ወይም ተቃዋሚዎች ጩኸት ህጋዊ ተቀባይነት የሌለዉ መሆኑን መረዳት እንችላለን፡፡

Advertisements
This entry was posted in Agaw Kemant. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s