የቅማንት ብሄረሰብ የራስ አስተዳደርን ሳይሸራረፍ ለማቋቋም የሚረዱ የህግ ማዕቀፎች፤ (Legal frameworks for Establishing Kemant Full Self-Rule)

በጥላሁን ጀምበር

1. መግቢያ

የቅማንት ብሄረሰብን የማንነትና ራስ አስተዳደር ጥያቄ ለማቅረብ ትልቁ የህግ ማዕቀፋችን የፌዴራሉ እና የአማራ ክልል ህገ-መንግስቶች በጋራ የደነገጉት አንቀፅ 39 እንደሆነ ግልፅ ነዉ፡፡ በፌዴራሉ ህገ-መንግስት አንቀፅ 39(5) እና በአብክመ ህገ-መንግስት አንቀፅ 39(7) መሠረት የቅማንት ብሄረሰብ እንደቅማንት መስፈርቶችን አሟልቶ በመገኘቱ ምክኒያት በሁለቱም መንግስቶች (በፌዴሬሽን ም/ቤት እና በአብክመ ም/ቤት) በኩል የማንነትም ሆነ የራስ አስተዳደር እዉቅና ያገኘ ስለሆነ አከራካሪ ጉዳይ አይደለም፡፡ ባሁኑ ወቅት የቅማንትን ብሄረሰብና የክልላችን መንግስት እያከራከረ የሚገኘዉ ጉዳይ የቅማንት ብሄረሰብ የራስ አስተዳደር እንዴት ይቋቋም ወይም ይከለል የሚለዉ ነዉ፡፡ ባንድ በኩል የቅማንት ብሄረሰብ እንደባለመብት የራስ አስተዳደሩ መከለል ያለበት የቅማንት ህዝብ ሰፍሮ በሚገኝበት አካባቢ ማለትም በ126 ቀበሌዎች የህዝብን ፍላጎት መሠረት አድርጎ መሆን ይገባዋል የሚል አቋምና ክርክር ሲያቀርብ በሌላ በኩል ደግሞ የክልላችን መንግስት የቅማንት ብሄረሰብ የራስ አስተዳደር መከለል ያለበት በ42 ቀበሌዎች ብቻ ነዉ በሚል አቋም ዉሳኔ አስተላልፏል፤ማስፈፀሚያ አዋጅም አፅድቋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለም የክልሉ መንግስት ባስተላለፈዉ ዉሳኔ መሠረት የቅማንትን ብሄረሰብ የራስ አስተዳደር በ42 ቀበሌዎች ብቻ ለማቋቋም ሲንቀሳቀስ ህዝባዊ ተቃዉሞ ገጥሞታል፡፡ ይህንን ህዝባዊ ተቃዉሞ በዴሞክራሲያዊና ሠላማዊ መንገድ ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ የኃይልና ጉልበት አማራጭ ዉስጥ ስለተገባ ከጥቅምት 24 ቀን 2008 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 29 ቀን 2008 ዓ.ም ባለዉ ጊዜ ዉስጥ በተደረገዉ የእርስ በርስ ጦርነት ምክኒያት ፍፁም አላስፈላጊ የሆነ የይህወት መስዋዕትነት ተከፍሏል፡፡ ይህንን ተከትሎም የፌዴራል መንግስት ፀጥታ አስከባሪ ኃይል ሠላም ለማስፈን ወደ አካባቢዉ መግባቱ አይዘነጋም፡፡ የአብክመ እና የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣኖች በተገኙበት ከቅማንት ብሄረሰብ ተወካዮች ጋር በ08/03/2008 ዓ.ም ጎንደር ዩኒቨርስቲ ሳይንስ አምባ አዳራሽ እና በ12/08/2008 ዓ.ም ደግሞ በባህር ዳር ከተማ አጠርቂ ዉይይቶች መካሄዳቸዉም ይታወሳል፡፡ በጥቅሉ ከሁለቱም ወሳኝ ዉይይቶች ማጠቃለያ እንደተረዳነዉ የቅማንት ብሄረሰብ የራስ አስተዳደር አከላለልን በሚመለከት ከ42ቱ ቀበሌዎች በተጨማሪ ሌሎች ቀበሌዎች የህዝብን ፍላጎት መሠረት በማድረግ ከተካተቱ በኋላ በ42 ቀበሌዎች ብቻ የቅማንትን የራስ አስተዳደር ለማቋቋም የክልሉ ም/ቤት ያፀደቀዉ አዋጅ ተሻሽሎ የቅማንት ብሄረሰብ የራስ አስተዳደር በተሟላ መንገድ ይመለሳል የሚል ቃል ተገብቷል፡፡ ይህን ተከትሎም በክላልችን መንግስት አመራሮች አስተባባሪነት ወይም መሪነት (ሁሉም ባይሆኑም) ቅማንትን ከምድረ-ገፅ የማጥፋት የፀረ-ኃይሎች ዘመቻ ተካሂዶ ታሪክ የማይረሳዉ ዘር የማጥፋት ዓለም አቀፍ ወንጀል ተፈፅሟል፡፡ ያም ሆነ ይህ የክልላችን መንግስት የቅማንት ብሄረሰብ ራስ አስተዳደር በ42 ቀበሌዎች ብቻ መጀመሪያ ካልተቋቋመ ከዚህ ቀደም የወጣዉን አዋጅ ወይም ህግ መፃረር ይሆናል በሚል ትርጉም ክርክሩን እያቀረበ ይገኛል፡፡ የራስ አስተዳደሩን በ42 ቀበሌዎች ብቻ ማቋቋም ተገቢ እንዳልሆነ የሚደግፉ የህግ ማዕቀፎች በሚከተለዉ መልክ ይቀርባሉ፡፡

2. የአብክመ እና የፌዴራል ህገ-መንግስቶች

ሁለቱም ህገ-መንግስቶች በጋራ አንቀፃቸዉ (አንቀፅ 39) የቅማንት ብሄረሰብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን መብቱ በማናቸዉም መልኩ ያለገደብ የተጠበቀ እንደሆነ እንዲሁም ብሄረሰቡ ራሱን ሲያስተዳድር የሚኖረዉ መብት “የተሸራረፈ ሳይሆን ሙሉ መብት” እንደሆነ በግልፅ ይደነግጋሉ፡፡ በተጨማሪም የዚህ መብት ሙሉነትም ከሚገለፅባቸዉ አብነቶች መካከልም የቅማንት ብሄረሰብ በሰፈረበት መልክዓምድር (a territory where kemant nationality is found to be settled) ራሱን የሚያስተዳድርበት መንግስታዊ ተቋማት (ም/ቤቶች፣ፍርድ ቤቶችና የአስተዳደር አስፈፃሚ አካላት) የማቋቋም እንዲሁም በክልልና ፌዴራል አስተዳደሮች ዉስጥ ሚዛናዊ ዉክልና የማግኘት መብቶችን የሚያካትት ስለመሆኑ ሁለቱ ህገ-መንግስቶች አስቀምጠዋል፡፡
የእነዚህን ህገ-መንግስቶች አንቀፅ 39 ወስደን ስንመለከት ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የተሸራረፈ እንዳልሆነ ነዉ፡፡ በብዙ ቀበሌዎች እና ጎጦች የቅማንት ብሄረሰብ በኩታ ገጠም ሰፍሮ የሚገኝ ሆኖ ሳለ ከህዝቡ ፍላጎትና ዉሳኔ ዉጭ በ42 ቀበሌዎች ብቻ የቅማንትን የራስ አስተዳደር ለማቋቋም መሞከር በራሱ ሁለቱ ህገ-መንግስቶች በግልፅ ካስቀመጡት ድንጋጌዎች ዉጭ መሆኑን እንረዳለን፡፡

3. አዋጅ ቁጥር 251/1993

በአብክመ እና በፌዴራል መንግስት ህገ-መንግስቶች የጋራ አንቀፅ 39 ስር የተቀመጡት የማንነትና ራስ አስተዳደር የብሄረሰብ መብቶች በጥቅሉ የተቀመጡ በመሆናቸዉ ዝርዝር ማስፈፀሚያ አዋጅ ቁጥር 215/1993 በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በኩል ወጥቶ ተግባራዊ እየተደረገ ነዉ፡፡ በዚህ አዋጅ አንቀፅ 19(1) ስር እንደተደነገገዉ የፌዴሬሽን ም/ቤት የብሄር፣ብሄረሰቦች እና ህዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን በተመለከተ በሚቀርቡ ጥያቄዎች ላይ ዉሳኔ የመስጠት ስልጣን እንደሚኖረዉ በግልፅ ያስቀምጣል፡፡ ይህ አዋጅ ከጠቀሳቸዉ መብቶች መካከል አንድ ብሄር፣ብሄረሰብ ወይም ህዝብ የራስ በራስ ማስተዳደር መብቴ ተሸራርፏል ብሎ ለሚመለከተዉ አካል የማቅረብ መብትን እንደሚጨምር ነዉ፡፡ ይህ መብትም ከላይ ለማየት እንደሞከርነዉ በሁለቱም ህገ-መንግስቶች የጋራ አንቀፅ 39 ስር ተደንግጎ የምናገኘዉ መብት ነዉ፡፡ የቅማንት ብሄረሰብ የራስ አስተዳደር ሲፈቀድም ሆነ ሲቋቋም በተሸራረፈ ሁኔታ መሆን እንደማይገባ እና በተሟላ መንገድ እንዲመለስና እንዲቋቋም የሚመለከተዉን የመንግስት አካል እንደመብት መጠየቅ እንደሚቻል ይህ አዋጅ ሙሉ ህጋዊ ድጋፍ እንደሚሰጥ መረዳት አያዳግትም፡፡

4. የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዉሳኔ

የፌዴራል ህገ-መንግስት አንቀፅ 62(3) እንዲሁም አዋጅ ቁጥር 251/1993 አንቀፅ 19(1) እና አንቀፅ 20(3) በግልፅ እንደሚደነግጉት የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን በሚመለከት በሚቀርቡ ጥያቄዎች ዙሪያ ዉሳኔ የመስጠት እና ጥያቄዉ ለሚመለከተዉ ክልል ም/ቤት ቀርቦ በሁለት ዓመት ጊዜ ዉስጥ ዉሳኔ ካልተሰጠዉ ወይም በተሰጠዉ ዉሳኔ ላይ ቅሬታ አለኝ የሚል ብሄረሰብ ጉዳዩን ለፌዴሬሽን ም/ቤት ማቅረብ እንደሚችልና በቀረበዉ ቅሬታ ላይም ም/ቤቱ ዉሳኔ መስጠት እንደሚችል ተቀምጧል፡፡ ይህንን የህግ ስነ-ስርዓት ተከትሎም የቅማንት ብሄረሰብ የአብክመ ም/ቤት ባስተላለፈዉ 42 ቀበሌዎችን ብቻ ያቀፈ የራስ አስተዳደር ዉሳኔ የተሸራረፈ ነዉ በሚል ቅሬታ ለፌዴሬሽን ም/ቤት ህጋዊ አቤቱታ በማቅረቡ ምክኒያት በጉዳዩ ላይ ሰኔ 17 ቀን 2007 ዓ.ም የመጨረሻ ዉሳኔ ተሰጥቷል፡፡ የዚህን የመጨረሻ ዉሳኔ አንድምታ አስተባባሪ ኮሚቴዉ እንደሚከተለዉ ተረድቶታል፡፡

4.1. የአብክመ ም/ቤት የሰጠዉን ዉሳኔ የፌዴሬሽን ም/ቤት ያፀደቀዉ ስለመሆኑ፤

የአብክመ ም/ቤት የሰጠዉን ዉሳኔ የፌዴሬሽን ም/ቤት ያፀደቀዉ ስለመሆኑ የመጨረሻ በሆነዉ ዉሳኔ ዉስጥ በሚከተለዉ አኳኋን ገልፆታል፤
“በቋሚ ኮሚቴዉ የቀረበዉ የዉሳኔ ሀሳብና የክልሉ መንግስት የሰጠዉ ዉሳኔ ተመሳሳይ ሆነዉ በመገኘታቸዉ የክልሉ ም/ቤት ለቅማንት ማህበረሰብ በህገ-መንግስቱ በተቀመጡት መስፈርቶች መሠረት የሰጠዉን የማንነት እዉቅናና የራስ አስተዳደር ም/ቤቱ ተቀብሎ አፅድቋል፡፡”

የዚህ ዉሳኔ ትርጉም በመሠረታዊነት የአብክመ ም/ቤት ለቅማንት ማህበረሰብ የሰጠዉ የማንነት እዉቅና (kemant identity recognition) ትክክለኛ በመሆኑ የፌዴሬሽን ም/ቤት በዉሳኔዉ ላይ ያገኘበት እንከን ስለሌለ ተቀብሎ እንዳለ ያፀደቀዉ ስለመሆኑ እንረዳለን፡፡ ካሁን ቀደም ቅማንት የለም የሚለዉ ዉሳኔ ወይም አስተሳሰብ በመርህ ብቻ ሳይሆን በተግባር በክልላችን መንግስት ዳግማዊ ዉሳኔ የተሻረ ስለመሆኑና የፌዴሬሽን ም/ቤትም ይህንን ትክክለኛ ዉሳኔ እንዳለ ተቀብሎ ያፀደቀዉ ስለመሆኑ መገንዘብ ይቻላል፡፡
አሁን ስራ ላይ ባለዉ ህገ-መንግስታዊ ስርዓታችን አግባብ የአንድ ማህበረሰብ የማንነት እዉቅና ከተሰጠ በኋላ ቀጥሎ የሚመጣዉና የማይቀረዉ ጥያቄ የራስ በራስ ማስተዳደር መብት እዉቅና ጥያቄ ነዉ (ህገ-መንግስት፣ አንቀፅ 39(5))፡፡ የማንነት እዉቅና የተሰጠዉ አንድ ማህበረሰብ ባብዛኛዉ በተያያዘ መልክዓምድር (predominantly contiguous territory) ሰፍሮ የሚገኝ ከሆነ ራሱን በራሱ የማስተዳደር የተሟላና ያልተሸራረፈ መብት ሁለቱም ህገ-መንግስቶች ያለገደብ ያጎናፀፉ ስለመሆናቸዉ እንረዳለን፡፡ ከዚህ መንፈስ ስንነሳ የአብክመ ም/ቤት የቅማንትን የራስ በራስ ማስተዳደር መብት በመርህ ደረጃ ተቀብሎ በተግባርም በ42 ቀበሌዎች ብቻ ብሄረሰቡ ራሱን በራሱ ማስተዳደር እንዲችል እዉቅና ሰጥቷል፤የፌዴሬሽ ም/ቤትም ይህንን ዉሳኔ ተቀብሎ ማፅደቁን መረዳት እንችላለን፡፡ የክልላችን መንግስት ም/ቤትና የፌዴሬሽን ም/ቤት እስከዚህ ድረስ የሄዱበት ርቀት ሲገመገም በእዉነቱ የሚደነቁና የሚመሰገኑ መሆናቸዉን እንረዳለን፡፡ የቅማንት ህዝብ በዚህ ረገድ ቅሬታ የለዉም፡፡ አስተባባሪ ኮሚቴዉም ካሁን ቀደም ለሚመለከታቸዉ የመንግስት አካላት በፃፋቸዉ ደብዳቤዎች የተሰማዉን የደስታ ስሜት በቅማንት ብሄረሰብ ስም ገልጿል፡፡

4.2. የቅማንትን የራስ አስተዳደር አከላለል በተመለከተ ሁለቱ ም/ቤቶች ያላቸዉ አቋም፤

የክልላችን መንግስት ለቅማንት ብሄረሰብ የማንነትና ራስ አስተዳደር እዉቅና ከሰጠ በኋላ አከላለሉን በሚመለከት ግን በ42 ቀበሌዎች ብቻ ይቋቋማል የሚል አቋም እንደያዘ የክልሉ ም/ቤት ከሰጠዉ ዉሳኔ መረዳት እንችላለን፡፡ ዛሬም ቢሆን ይህ አቋም የተለወጠ አይመስለንም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አስተባባሪ ኮሚቴዉ ቀሪ ቀበሌዎችና ጎጦች ተካተዉ የቅማንት ብሄረሰብ የራስ አስተዳደር መቋቋም ይገባዋል በሚል ዘርዝሮ ባቀረበዉ ቅሬታ መሠረት የፌዴሬሽን ም/ቤት የሚከተለዉን ዉሳኔ ሰጥቷል፤
“በማህበረሰቡ አስተባባሪ ኮሚቴ በኩል የእራስ አስተዳደሩን አከላለል በተመለከተ የቀረበዉን ቅሬታ በተመለከተ የክልሉ ም/ቤት ዋናዉን ጥያቄ ለመመለስ በሄደበት አግባብ እንዲፈታዉ ወስኗል፡፡”

ከዚህ ዉሳኔ መረዳት እንደምንችለዉ የፌዴሬሽን ም/ቤት አቋም የክልላችን መንግስት ካሁን በፊት የቅማንትን የራስ አስተዳደር እዉቅና ሰጥቶ በተግባር በ42 ቀበሌዎች እንዲቋቋም ማድረግ ከቻለ ቅሬታ የቀረበባቸዉን ቀበሌዎችና ጎጦች እንደገና አይቶ የራስ አስተዳደሩን ማቋቋም ይችላል፤ስለሆነም የክልሉ ም/ቤት ዋናዉን ጥያቄ ለመመለስ በሄደበት አግባብ እንዲፈታዉ የሚል ዉሳኔ መስጠቱን እንረዳለን፡፡ ይሁን እንጂ የክልላችን ም/ቤት በቅማንት ብሄረሰብ በኩል የቀረበዉን ቅሬታ እና የፌዴሬሽን ም/ቤት የሰጠዉን ዉሳኔ ሳይመለከት ቀደም ሲል የቅማንት ራስ አስተዳደር በ42 ቀበሌዎች ብቻ እንዲቋቋም የሰጠዉን ዉሳኔ አፅድቆ ማቋቋሚያ አዋጅ አዉጥቷል፡፡

4.3. የፌዴሬሽን ም/ቤት ዉሳኔ አስገዳጅ ስለመሆኑ፤

አዋጅ ቁጥር 251/1993 አንቀፅ 56 በግልፅ እንደሚደነግገዉ የፌዴሬሽን ም/ቤት የሚሰጠዉ ዉሳኔ የመጨረሻ በመሆኑ እና ጉዳዩ የሚመለከታቸዉ ወገኖች ዉሳኔዉን የማክበርና የመፈፀም ግዴታ እንዳለባቸዉ መረዳት እንችላለን፡፡ ከዚህ የህግ ድንጋጌ ጋር አብሮ በሚሄድ መንገድ የፌዴሬሽን ም/ቤት የሚከተለዉን ዉሳኔ ሰጥቷል፤

“የሚመለከታቸዉ የክልሉ የተለያዩ የመንግስት አካላትም ምክር ቤቱ ያሳለፋቸዉን የመጨረሻ ዉሳኔ እንዲፈፅሙና እንዲያስፈፅሙ፣ የማህበረሰቡ አስተባባሪ ኮሚቴም ከክልሉ መንግስት ጋር ተቀራርቦ በመስራት የም/ቤቱን ዉሳኔ በመፈፀምና በማስፈፀም የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ” የሚል ነዉ፡፡

ከዚህ ላይ መዘንጋት የማይገባን ቁም ነገር ቢኖር የቅማንት አስተባባሪ ኮሚቴ ህዝቡ የወከለዉ እና አዋጅ ቁጥር 251/1993 አንቀፅ 21(2) በሚደነግገዉ አግባብ ህጋዊ መሠረት ያለዉ ስለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ከክልላችን መንግስት አመራሮች ጋርም በዉክልና ይዞት ከሚንቀሳቀሰዉ ህገ-መንግስታዊ ጥያቄ አንፃር የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ልዩነት የሌላቸዉና ሁሉም ለተመሳሳይ ዓላማ መስራት የሚገባቸዉ መሆኑን ነዉ፡፡ የፌዴሬሽን ም/ቤትም የህግና የፖለቲካ ዉሳኔ ሰጭ ተቋም እንደመሆኑ መጠን የቅማንት አስተባባሪ ኮሚቴና የክልላችን መንግስት አካላት (ም/ቤት፣ አስፈፃሚ አካላት፣ ፍ/ቤቶች) ም/ቤቱ የሰጠዉን ዉሳኔ በጋራ ተቀራርበዉ መፈፀምና ማስፈፀም እንደሚጠበቅባቸዉ ያስተላለፈዉ ዉሳኔ በእጅጉ አግባብነት አለዉ ብለን እናምናለን፡፡

4.4. የፌዴሬሽን ም/ቤት የወሰነዉን ዉሳኔ ማስፈፀም የሚገባዉ ስለመሆኑ፤

የፌዴራሉ ህገ-መንግስት አንቀፅ 62(3) እንዲሁም አዋጅ ቁጥር 251/1993 አንቀፅ 19(1) እና አንቀፅ 20(3) በግልፅ እንደሚደነግጉት የራስን ዕድል በእራስ የመወሰን መብትን በሚመለከት በሚቀርቡ ጥያቄዎች ዙሪያ ዉሳኔ የመስጠት እና ጥያቄዉ ለሚመለከተዉ ክልል ም/ቤት ቀርቦ በሁለት ዓመት ጊዜ ዉስጥ ዉሳኔ ካልተሰጠዉ ወይም በተሰጠዉ ዉሳኔ ላይ ቅሬታ አለኝ የሚል ብሄረሰብ ጉዳዩን ለፌዴሬሽን ም/ቤት ማቅረብ እንደሚችልና በቀረበዉ ቅሬታ ላይም ም/ቤቱ ዉሳኔ የመስጠት ስልጣን እንዳለዉ ተመልክተናል፡፡ በዚህ ህግ አግባብ የፌዴሬሽን ም/ቤት የቅማንትን ብሄረሰብ የራስ አስተዳደር አከላለል አፈፃፀምን በሚመለከት የሚከተለዉን ዉሳኔ አስተላልፏል፤

“የሚመለከታቸዉ የም/ቤቱ ቋሚ ኮሚቴና ጽ/ቤቱም የዉሳኔዉን አፈፃፀም በተመለከተ ተገቢዉን ክትትል እንዲያደርጉ ወስኗል፡፡”

ከዚህ ዉሳኔ መንፈስ መረዳት እንደሚቻለዉ የፌዴሬሽን ም/ቤት የቅማንትን ብሄረሰብ የራስ አስተዳደር አፈታት በተመለከተ የሰጠዉ ዉሳኔ በመጀመሪያ ደረጃ በቅማንት አስተባባሪ ኮሚቴ እና በክልላችን መንግስት መከበርና መፈፀም ያለበት ቢሆንም ይኸዉ ሳይሆን ቢቀር ግን የፌዴሬሽን ም/ቤት የዉሳኔዉን አተገባበር አስመልክቶ ክትትልና ቁጥጥር ከማካሄድ አልፎ ጣልቃ ገብቶ ዉሳኔዉን የማስፈፀም ስልጣንና ህገ-መንግስታዊ ኃላፊነት እንዳለበት ነዉ፡፡ የክልላችን መንግስት የቅማንት ብሄረሰብ አስተባባሪ ኮሚቴ የራስ አስተዳደሩን አከላለል በተመለከተ ያቀረበዉን ቅሬታ ሳይቀበል በ42 ቀበሌዎች ብቻ አስተዳደሩን ለማቋቋም አቋም በያዘ ጊዜ ወይም በማንኛዉም ሁኔታ የራስ አስተዳደሩን አከላለል በሚመለከት በሁለቱም ወገን የፌዴሬሽን ም/ቤት በሰጠዉ ዉሳኔ አግባብ ለመፈፀምና ለማስፈፀም ስምምነት በማይኖርበት ወቅት የፌዴሬሽን ም/ቤት ጣልቃ ገብቶ ጉዳዩን ባግባቡ እንዳይፈታ የሚያደርግ የህግ ስርዓት የለም ብለን እናምናለን፡፡ በቀጣይ ደግሞ የቅማንት ብሄረሰብ ልዩ ወረዳ ማቋቋሚያ አዋጅን በሚመለከት ዝርዝር ትንታኔ ይዘን እንቀርባለን፡፡ ቸር ይግጠመን!

Advertisements
This entry was posted in Agaw Kemant. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s