Genocide Continues against Kemant People in Ethiopia, North Gondar to Stop Constitutional Demand for Self-Rule

by Tilahun Jember
የደርግ መረን የለቀቀ ፋሽታዊ አገዛዝ የኢትዮጵያን ብሄር-ብሄረሰቦች አንገፈገፈ፡፡ ግፉም ብሄር-ብሄረሰቦችን ቆርጠዉ ለመብታቸዉ እንዲታገሉ ገፋቸዉ፡፡ ትግሉም በምሁሩ ተመራ፡፡ ዩኒቨርስቲዎች ሳይቀሩ የትግል መፈልፈያ ሆኑ፡፡ ምሁራን ከዩኒቨርስቲ ትምህርታቸዉን እያቋረጡ ወደ ጫቃ መግባት ግድ ሆነባቸዉ፡፡ ገበሬዉም ዋናዉ የትግሉ አካል ሆነ፡፡ ይህ ነዉ የማይባል የእርስ በርስ ጦርነት ተካሄደ፡፡ በቃላት የማይገለፅ በሰዉና ንብረት የሚገመት መስዋዕት ተከፈለ፡፡ በመጨረሻም አምባገነን የደርግ አገዛዝ በሰፊዉ ህዝብ ተጋድሎ ተገረሰሰ፡፡ ኢህአዴግም አዲሱን ስልጣን ተረከበ፡፡ የሽግግር ቻርተር ፀደቀ፡፡ የብሄር-ብሄረሰቦች መብት ትልቅ እዉቅና በሽግግሩ ቻርተር ተሰጠዉ፡፡ አዋጅ ቁጥር 7/1984 ክልሎችን አዋቀረ፡፡ በዚህ አዋጅ መሠረት ክልሎች ሲዋቀሩ ከብሄር-ብሄረሰብ መብት ፅንሰ-ሃሳብ ሳይወጣ ነገር ግን ለተወሰኑት ብሄር-ብሄረሰብ ህጋዊ እዉቅና ሲቸር ለቀሪዎች ደግም ቅማንትን ጨምሮ አይመለከታቸዉም ተባለ፡፡ ቀጥሎም አሁን በስራ ላይ ያለዉ የፌዴራሉ ህገ-መንግስት በ1987 ዓ.ም ፀደቀ፡፡ አብዛኛዉ የህገ-መንግስቱ ክፍል ስለ ብሄር-ብሄረሰቦች መብትና እዉቅና ያወራል፡፡ ካለብሄር-ብሄረሰቦች መብት እዉቅናና መከበር ዉጭ ኢትዮጵያ ምንም አይደለችም በሚለዉ ፍልስፍና የተቀረፀ ህገ-መንግስት ሆነ፡፡ ይህ ህገ-መንግስትም በአንቀፅ 39 እና 47 ስር ብሄር-ብሄረሰቦች ያላቸዉን ገደብ የለሽ መብት (ተገንጥለዉ የራሳቸዉን ልዑላዊ አገር እስከመፍጠር ድረስ) ሰጠ፡፡ የፌዴሬሽን ም/ቤትም ዋና የቤት ስራዉ በብሄር-ብሄረሰቦች መብት መከበር ላይ ያጠነጠነ እንዲሆን ስልጣንና ተግባር ተሰጠዉ፡፡
የስልጤ ብሄረሰብ የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄ በ1992 ዓ.ም ገደማ አቀረበ፡፡ የራስ አስተዳደር ጥያቄን በተመለከተ እንዴት እንደሚመለስ ህገ-መንግስቱ በቂ ምላሽ የሚሰጥ ቢሆንም ማንነትን በተመለከተ ግን ቀጥተኛና ግልፅ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አንድም አንቀፅ ከህገ-መንግስታችን ጠፋ፡፡ በኋላም የህገ-መንግስት አጣሪ ጉባኤ (council of constitutional inquiry) እያንዳንዱን የህገ-መንግስት አንቀፅ አገላበጠ፡፡ ህገ-መንግስታዊ ትርጉም ሰጠ፡፡ ለማንነት እዉቅና ሳይሰጥ ወይም የማንነት ጥያቄ መጀመሪያ ሳይመለስ የራስ አስተዳደር ጥያቄ ሊመለስ አይችልም የሚል ድምዳሜ ላይ ተደረሰ፡፡ የስልጤን ብሄረሰብ የማንነትም ሆነ የራስ አስተዳደር ጥያቄ የደቡብ ብሄር-ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት ባግባቡ መፍታት ስላቃተዉ በቀረበዉ ጥያቄና ቅሬታ ላይ የፌዴሬሽን ም/ቤት በሰፊዉ መከረ፡፡ ከዚያም አቅጣጫ አዘል ዉሳኔ በማሳረፍ የደቡብ ክልል መንግስት ራሱ የቀረበለትን ጥያቄ እንዲመልስ ተባለ፡፡ ነገሩ አልሆን ብሎ ደም አፋሳሽ ግጭት ካስከተለ በኋላ የህዝበ-ዉሳኔ (refurrendum) መብት እንደአማራጭ ተቀባይነት አገኘ፡፡ የስልጤ ህዝብ በሚስጥር ድምፅ እንዲሰጥ ተደረገ፡፡ በመጨረሻም የስልጤ ብሄረሰብ ዉስጣዊ ነፃነቱን በህዝበ-ዉሳኔ አረጋገጠ፡፡ በወቅቱም የስልጤን ብሄረሰብ መብት አንግበዉ ሲንቀሳቀሱና ሲያንቀሳቅሱ የነበሩ ታጋዮች (ለምሳሌ ሬድዋን ሁሴን) የስርዓቱ ዋና ደጋፊዎች ናቸዉ ተባሉ፡፡ በብልሃተኛዉ ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ (አፈር ይቅለላቸዉና) አመራር ሰጭነት እንደነ ሬድዋን ሁሴን ላሉት የስልጤ መብት ታጋዮች በፌዴራል ደረጃ ቁልፍ የአመራር ቦታ ተሰጣቸዉ፡፡
የስልጤን የማንነትና ራስ አስተዳደር ጥያቄ ተከትሎም አዋጅ ቁጥር 251/1993 በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ፀደቀ፡፡ ይህ አዋጅ ህገ-መንግስቱ ያልመለሳቸዉን በስልጤ ህዝብ ጥያቄ ወቅት የተነሱትን ጉዳዮች በሚመልስና ወደ ፊት በማንኛዉም ህዝብ በኩል ሊነሳ የሚችለዉን የማንነትና ራስ አስተዳደር ጥያቄ ለማስተናገድ የሚያስችሉ ስነ-ስርዓቶችን የያዘ ህግ ሆኖ ተቀረፀ፡፡ በአማራ ክልል ዉስጥም የአርጎባ ብሄረሰብ በዚህ አዋጅ መሰረት የማንነትና ራስ አስተዳደር ጥያቄ አቀረበ፡፡ ክልሉም በአዋጅ ቁጥር 130/1998 መሠረት የአርጎባን ብሄረሰብ የማንነትና ራስ አስተዳደር ጥያቄ ሙሉ በሙሉ መለሰ፡፡
የቅማንት ብሄረሰብ የማንነትና ራስ አስተዳደር ጥያቄም አዋጅ ቁጥር 251/1993 ባስቀመጣቸዉ መስፈርቶች መሠረት ለክልሉ መንግስት ቀረበ፡፡ በእየደረጃዉ የሚገኙ የክልል መንግስት አካላት ጥያቄዉን የጎሪጥ ተመለከቱት፡፡ ናቁትም፡፡ ቅሜም እንኳን የጥያቄዉን መንገድ አገኘሁት እንጂ ላልመለስ ማሃላ አለኝ ብሎ ትግሉን ቀጠለ፡፡ የትግሉን መስመርም በሰላማዊ፣ዴሞክራሲያዊና ህጋዊ መርሆች ላይ የተመሠረተ አደረገ፡፡ ሁሌም በጡንቻና በጠመንጃ ከሚታመንበት እና የትምክህት አስተሳሰብ ስር ሰዶ የገነገነበት አገረ-ጎንደር ላይ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሠላማዊ ትግል (non-violent struggle) ልምምድ ተካሄደበት፡፡ ሠላማዊ ትግሉ እየገፋ ሲመጣ የአማራ ክልል መንግስት በስዉርም ሆነ በግላጭ ማፈን ጀመረ፡፡ የተሞከሩ የአፈና ስራዎች ወይም ሴራዎች ሁሉ በሰላማዊ ትግል ስልት ከሸፉ፡፡ የክልሉ መንግስትም ለቅማንት የማንነትና ራስ አስተዳደር ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት አራት (4) ጊዜ አስጠና፡፡ በመጨረሻም አይደለም የራስ አስተዳደር ጥያቄዉ ሊመለስ ቀርቶ የማንነት ጥያቄዉም ተድበስብሶ ተወሰነ፡፡
የቅማንት ህዝብም በሠላማዊና ህጋዊ ትግል ያምናልና አዋጅ ቁጥር 251/1993 በሚያስቀምጠዉ መሠረት ለፌዴሬሽን ም/ቤት የቅሬታ ይግባኝ አቀረበ፡፡ የፌዴሬሽን ም/ቤት በይግባኙ ላይ ምላሽ ለመስጠት ዘገዬ፡፡ የቅሬታ ሰላማዊ ሰልፎች መካሄድ ጀመሩ፡፡ ጀግናዉ የጭልጋ ህዝብ አይከል ከተማን በማጥለቅለቅ የነበረዉን የፍርሃት ድባብ ሰበረዉ፡፡ ቀጥሎም በታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ መላዉ የቅማንት ህዝብ የተሳተፈበት አስደናቂ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሄደ፡፡ አሞተ ኮስታራዉ የአርማጭሆ ህዝብ ጎንደር ላይ የተደረገዉን ሰላማዊ ሰልፍ ለማድመቅ ሌሊቱን ሁሉ በእግሩ ሲጓዝ አደረ፡፡ እነዚህን ሠላማዊ ሰልፎች ተከትሎ የፌዴሬሽን ም/ቤት አጥኚ ቡድን አዋቅሮ ወደ ቅማንት ክልል ላከ፡፡ የተላከዉ አጥኚ ቡድንም የአጠናን ስርዓትን ተከትሎ ፍፁም ገለልተኛ በሆነ መንገድ በቅማንት ህዝብ ክልል ዉስጥ እያጠና ባለበት ወቅት በአማራ ክልል መንግስት ዉስን ባለስልጣናት ሴራ በላይ አርማጭሆ ወረዳ ትክል ድንጋይ ከተማ ለበርካታ ዓመታት ተተክሎ የቆዬን በቅማንትኛ ቋንቋ እንኮ ዳንግዝቲዉ–እንኳን ደህና መጣችሁ በሚል የተፃፈን ታፔላ እንዲነቀል በማድረግ ህዝቡን ስሜት ዉስጥ እንዲገባ አድርገዉ አመፅ አስነሱ፡፡ ይህን አመፅ ሰበብ አድርገዉ በጅምላ የቅማንትን ኮሚቴ አባላት በሌሊት አሳፍነዉ ከቅማንት ክልል ዉጭ ወስደዉ ደባርቅ ወረዳ ላይ አሰሩ፡፡ በተመሳሳይ ወቅት ጭልጋ ወረዳ ላይ የፌዴሬሽን ም/ቤት አጥኚ ቡድን ጥናቱን ለማካሄድ በዝግጅት ላይ እንዳለ የኮሚቴ አባላትን ግፍፍ አድርገዉ ዳባት ወረዳ ላይ እንዲታሰሩ አደረጉ፡፡ በዚህ ወቅትም መተማ ወረዳ ላይ አስጨናቂ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሄ፡፡ በርካታ የኮሚቴ አባላትና ሌሎች የሰልፉ ተሳታፊዎች ተጋፈዉ ደረቅ ጣቢያ ላይ ታስረዉ ስቃያቸዉን አዩ፡፡ የፌዴሬሽን አጥኚ ቡድንም የገጠመዉን ፈተና (challenge) ተጋፍጦ ጥናቱን አጠናቆ ተመለሰ፡፡ ይህ አጥኚ ቡድንም በቅማንት ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለዉን የማንነት ጭቆናና አፈና ባይኑ ተመልክቶ ተመለሰ፡፡
በጅምላ ያለምንም ወንጀል የታሰሩት ቅማንቶች ያለምንም ፍትሃዊ ፍርድ በስቃይ ማቀቁ፡፡ ቀሪዉ ያልታሰረዉ የቅማንት ኮሚቴ ቅሬታ የሚያሰማ ቡድን በፍጥነት አቋቁሞ ስራዉን ጀመረ፡፡ ቅሬታ የሚያሰማዉ ቡድንም ከዞን ጀምሮ እስከ ፌዴራል ድረስ ተንቀሳቀሰ፡፡ ክልል ላይ በተለያየ ምክኒያት ጀሮ የሚሰጥ አካል ባይገኝም ፌዴራል መንግስት ላይ ግን ተስፋ የሚሰጥ ነበር፡፡ ለሚመለከታቸዉ የፌደራል መንግስት አካላት ሁሉ የቅማንት ህዝብ ጥያቄ ህገ-መንግስታዊ እንደሆነ፣ትግሉ በሠላማዊና ህጋዊ መንገድ ብቻ እየተመራ እንደሆነ፣ በቅማንት ህዝብ ላይ በማንነቱ ምክኒያት እየደረሰበት ያለዉን ግፍ የፌዴሬሽን ም/ቤት አጥኚ ቡድን ሊመሰክረዉ እንደሚችልና ያለአግባብ በጅምላ ታፍነዉ ከቀያቸዉ ዘመድ አዝማድ ከማይጠይቃቸዉ ቦታ ተወስደዉ የታሰሩ ቅማንቶች እንዲፈቱ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲሰጠዉ አቤቱታ ቀረበ፡፡
ከትንሽ ቀናት በኋላ ያላግባብ የታሰሩ ልጆቻችን ይፈቱ በሚል በተማሪዎች የተመራ ድንገተኛ ህዝባዊ አመፅ ጭልጋ ወረዳ ላይ ፈነዳ፡፡ የቅማንት ህዝብ ተወካዮች ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ከክቡር ገዱ አንዳርጋቸዉ ጋር ባህር ዳር ከተማ ላይ በወቅቱ ጉዳይ ላይ በተመሳሳይ ቀን ዉይይት አካሄዱ፡፡ ከብዙ ዉይይት በኋላ ጎንደር ከተማ ላይ ከቅማንት ህዝብ ተወካዮች ጋር በቀጣይ ሳይዉል ሳያድር የጋራ ዉይይት እንደሚደረግ አቶ ገዱ አንዳርጋቸዉ ቃል ገቡ፡፡ በማሃል ተራ በተራ የታሰሩ ቅማንቶች እንዲፈቱ ተደረገ፡፡
ቃል በተገባዉ መሠረትም አቶ ገዱ አንዳርጋቸዉ ከቅማንት ተወካዮች፣ከመንግስት አመራሮችና ከሌሎች ብሄር-ብሄረሰቦች ተወካዮች ጋር አንድ ቀን የፈጀ የጋራ ዉይይት በጎንደር ከተማ ጎንደር ዩኒቨርስቲ ሳይንስ አምባ አዳራሽ ተደረገ፡፡ በዚህ ዉይይት በርካታ ሃሳቦች ተነሱ፡፡ የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ግዛት አብዩ ምንም አይነት ሃሳብ ሳይሰጡ ወጡ፡፡ የጭልጋ ወረዳ፣የላይ አርማጭሆ ወረዳና የመተማ ወረዳ አመራሮች በወረዳ አካባቢ የሚገኙትን የቅማንት አስተባባሪ ኮሚቴ አባላትን አጥብቀዉ በማዉገዝ ያለባቸዉን የአመራር ግድፈት ለመሸፋፈን ሞከሩ፡፡ ህግ የማስከበር ግዴታ እንዳለባቸዉ በመግለፅ ቅማንቶችን እንዲታሰሩ ማድረጋቸዉን ጭምር በማረጋገጥ ሞገቱ፡፡ የቅማንት ተወካዮችም በበኩላቸዉ ከዞን እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ አመራሮች የሚፈፅሙት ኢ-ህገመንግስታዊ ድርጊት እንጅ የቅማንት ጥያቄ በሠላማዊና ህጋዊ ትግል አግባብ እየተመራ መሆኑን ተከራከሩ፡፡ ከሌሎች ብሄር-ብሄረሰቦች ተወካዮች በኩልም ሚዛናዊ የሆኑ አስተያየቶች ተሰጡ፡፡ መንግስት የቅማንቶችን ህገ-መንግስታዊ ጥያቄ ሳይዉል ሳያድር እንዲመልስ፤የቅማንት አስተባባሪ ኮሚቴም ያለአግባብ የሚንቀሳቀሱ አባላትን በማረም በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ትግሉን እንዲመራ አሳሰቡ፡፡ በመጨረሻም አቶ ገዱ አንዳርጋቸዉ በመደምደሚያቸዉ የተነሳዉ የቅማንት የማንነት ጥያቄ ህገ-መንግስታዊ እንደሆነ፣ በህግና ስርዓት መመራት እንዳለበትና በእየደረጃዉ የሚገኙ የመንግስት አመራሮችም አብዛኛዎቹ የቅማንት ኮሚቴ አባላት ጥሩዎች በመሆናቸዉ አብረዉ በጋራ መስራት እንዳለባቸዉ አሳስበዉ ዉይይቱ ተቋጨ፡፡
የፌዴሬሽን ም/ቤት አጥኚ ቡድንም ያጠናዉን ጥናት ከከለሰ በኋላ ለተጨማሪ መረጃ ስብሰባ ወደ ቅማንት ህዝብ አካባቢ ለመሄድ በዝግጅት ላይ እንዳለ የክልሉ መንግስት ጣልቃ በመግባት እኔዉ ራሴ ለቀረበዉ ጥያቄ የፖለቲካ መፍትሄ እሰጠዋለሁ በሚል ስትራቴጅ በይግባኝ የፌዴሬሽን ም/ቤት ይዞት የነበረዉን ጉዳይ መልሶ በእጁ እንዲገባ አደረገ፡፡ በዚሁ ወቅት የተማሪዎች ትምህርት የመዝጋት አመፅ እና የገበሬ ጠገነ ወለላዉ በግፍ መገደል ከባድ ዉጥረት ፈጠረ፡፡ ከዚያም በአቶ ገዱ አንዳርጋቸዉ ሰብሳቢነት አሁንም በተለመደዉ በጎንደር ዩኒቨርስቲ ሳይንስ አምባ አዳራሽ ከቅማንት ህዝብ ተወካዮች፣ ከአማራ ህዝብ ተወካዮችና ከመንግስት አመራሮች ጋር አንድ ቀን የፈጀ ዉይይት ተካሄደ፡፡ አቶ ገዱ አንዳርጋቸዉም ብአዴን እንደ ድርጅት ራሱን ገምግሞ ለቅማንት ህዝብ የራስ አስተዳደር ጥያቄ ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት እንደወሰነ አስታዉቀዉ አምስት የመፍትሄ ሃሳቦችን አቀረቡ፡፡ አምስቱ የፖለቲካ የመፍትሄ ሀሳቦችም የሚከተሉት ነበሩ፤
1. በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 39 ስር የተቀመጡት መስፈርቶች ሙሉ በሙሉ ባይሟሉም የቅማንትን ማንነት እዉቅና መስጠት፤ቋንቋዉ፣ባህሉና ታሪኩ እንዲያድግ ማድረግ፤ዉክልና እንዲያገኝ ማድረግ፣
2. የራስን በራስ ማስተዳደር መብት ማስቻል፤ኩታ-ገጠም በሆኑባቸዉ ቦታዎች ማለትም ጭልጋና ላይ አርማጭሆ ወረዳዎችን መነሻ በማድረግ ሌሎችን ቦታዎች በተመለከተ ህዝቡን በማወያዬት የራስ አስተዳደር መፍቀድ፣
3. የራስ አስተዳደሩን ህዝቡ በብቃት ተወያይቶበት እንዲቋቋም ማድረግ፤ክልል ም/ቤት በአዋጅ እንዲመልስ ማድረግ፣
4. ህግና ስርዓትን በጥብቅ መቆጣጠር፤ ፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃ መዉሰድ፣
5. በአማራና በቅማንት ህዝብ መካከል የሚኖረዉን መልካም ግንኙነት ማጠናከር፣
ከዉይይቱ በኋላም በእነዚህ አምስት የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ ስምምነት ተደርሶ ለተግባራዊነታቸዉም እጅ ለእጅ በመያያዝ ቃለ-መሃላ ተፈፅሞ ተደመደመ፡፡ በክልሉ መገናኛ ብዙኃን በኩል አቶ ገዱ አንዳርጋቸዉ ስምምነት በተደረሰባቸዉ ነጥቦች ላይ ህዝባዊ መግለጫ ሰጡ፡፡ የቅማንትን የራስ አስተዳደር ለማቋቋምም የክልሉ መንግስት ብቻዉን ማስፈፀሚያ ማንዋል ቀርፆ ወደ ተግባር ገባ፡፡ የቅማንት አስተባባሪ ኮሚቴ በክልሉ መንግስት ላይ ትልቅ እምነት አሳደረ፡፡ በመሆኑም አምስቱን ስምምነት የተደረሰባቸዉን የፖለቲካ መፍትሄዎች ተግባራዊ በማድረግ ረገድ የቅማንት አስተባባሪ ኮሚቴ ከጨዋታ ዉጭ ተደረገ፡፡ በእየቀበሌዉ ከህዝብ ጋር ዉይይት ተጀመረ፡፡ የቅማንት ኮሚቴ አባላት ያለባቸዉን ህዝባዊ አደራና ኃላፊነት ተጠቅመዉ ስምምነቱ ባግባቡ እንዲፈፀም ለማድረግ በሚደረጉት ህዝባዊ ዉይይቶች ላይ ተገኝተዉ ሃሳባቸዉን ገለፁ፡፡ የመንግስት አመራሮች ግን በተቃራኒዉ የቅማንት ኮሚቴ ከዛሬ ጀምሮ ፈርሷል፤ የክልሉ መንግስት ጥያቄዉን የመለሰ በመሆኑ ባፈፃፀሙ ሂደት አስተባባሪ ኮሚቴዉ አይመለከተዉም የሚል ፕሮፓጋንዳ ለህዝቡ አሰራጩ፡፡
ይህን ተከትሎም “የአማራ ተወላጆች ህብረት አስተባባሪ” የሚባል አፍራሽ ኃይል ተቋቁሞ በይፋ ህገ-ወጥ የሆኑ የቅማንትን ህዝብን እንደ ህዝብ የሚያዋረዱ ንግግሮች፣ዛቻዎች፣ ስድቦችና ትንኮሳዎች እንዲፈፅምና እንዲያስፈፅም በመንግስት አመራሮች በኩል ዕድል መስጠት ብቻ ሳይሆን ድጋፍም ተደረገለት፡፡ በርካታ የቅማንት ንፁህ አርሶ አደሮች፣አርብቶ አደሮች፣ ነጋዴዎችና የመንግስት ሠራተኞች (በግምት ከ400 በላይ) ቅማንት በመሆናቸዉ ብቻ ገና ህገ-መንግስታዊ መብታቸዉ ሊከበርላቸዉ ነዉ በሚል ሰይጣናዊ ቅናት ወይም ምክኒያት የሌለዉ ስጋት ሳቢያ የአካላዊ ደህንነት መብታቸዉ ተጣሰ፤ንብረታቸዉ ያለአግባብ ተዘረፈ (ወደመ)፤ከስራ ገበታቸዉ ተፈናቅሉ፡፡ ይህ ሲሆን የክልሉ መንግስት እንደመንግስት የዚህ ህገ-ወጥና ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ተግባር ሰለባ የሆኑ ተጎጂዎች ህጋዊ ጥበቃ የሚያገኙበትን ፈጣን እና ፍትሃዊ እርምጃ አልወሰደም ነበር፡፡ ወንጀል ፈፃሚዎችንም ለህግ እንዲቀርቡ ሳያደርግ ቀረ፡፡
ከአምስቱ የመፍትሄ ሃሳቦች መካከል “በአማራና በቅማንት ህዝብ መካከል የሚኖረዉን መልካም ግንኙነት ማጠናከር” እንደሚገባ ስምምነት ላይ የተደረሰ ቢሆንም በቅማንት ህዝብ ማንነት ላይ ያነጣጠሩ ሰበ-ነክ ቅስቀሳዎችና ህገ-ወጥ እርምጃዎችን ተከትሎ ሊፈጠር የሚችለዉ ጉንጭ አልፋ ግጭትና ጥፋት ከባድ ቢሆንም በቅማንት ህዝብ በኩል በታየዉ እልህ አስጨራሽ ትዕግስት እና ሆደ-ሰፊነት ግፋ ሲልም በአገር ሽማግሌዎች ጥረት ምክኒያት ሊበርድ ችሏል፡፡
ከአምስቱ የመፍትሄ ሃሳቦች መካከል እጅግ የዴሞክራሲን መርህ የተከተለዉና በቅማንትና አማራ ህዝቦች መካከል የሚኖረዉን የወደፊት ግንኙነት ይበልጥ ያጠናክረዋል ተብሎ የሚታመነዉ የመፍትሄ ሃሳብ “የቅማንት የራስ አስተዳደር ሲመከለል ህዝባዊ ዉሳኔ ማክበር” የሚለዉ ቢሆንም ገና ከጅምሩ ፅንፈኛ ኃይሎች እንዲፈጠሩ በማድረግ ሁለቱም ህዝቦች የጥያቄዉን ህገ-መንግስታዊነት ብሎም ስምምነት የተደረሰባቸዉን አምስቱን የመፍትሄ ሃሳቦች በነፃነት እንዲረዱት ከተደረገ በኋላ የመሰላቸዉን እንዲወስኑ ማድረግ የተገባ ሆኖ ሳለ በተቻለ መጠን በቅማንት አስተዳደር ስር ሊካተት የሚገባዉን የመሬት ግዛት ማሳነስ (diminishing kemant territory) በሚል የተሳሳተ ስሌት ዉስጥ በመግባት አላስፈላጊ ዉጥረቶችን በመፍጠር ጊዜንና ጉልበትን በማቃጠል ጥያቄዉ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ባግባቡ እንዳይመለስ ማራዘም ብቻ ሳይሆን በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከከል ለዘመናት የኖረዉን መልካም ግንኙነት እንዲሻክር የሚያደርግ ተግባር በአስፈፃሚነት ግንባር ቀደም ተሳታፊ በሆኑ ዉስን የመንግስት አመራሮች በኩል ተፈፀመ፡፡
የቅማንት ህዝብ ህገ-መንግስታዊ ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ አዋጅ ቁጥር 251/1993 (አንቀፅ 21(2)) በሚፈቅደዉ መሠረት መስፈርቶችን አሟልቶ የህዝብ ይሁንታና ዉክልና አግኝቶ ሠላማዊ፣ ህጋዊና ዴሞክራሲያዊ መርሆችን በመከተል የሰላማዊ ትግል አማራጮችን በመጠቀም የወከለዉን ህዝብ ጥያቄ በጥንቃቄና ባግባቡ በመምራት “የጉልበትና የትምክህት አስተሳሰብ ስር ሰዶ በሚገኝባት ጎንደር ግዛት” ዉስጥ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ የበላይነቱን እንዲይዝ በሚያስችል መልኩ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ የሚገኝ ኮሚቴ መሆኑ ተካደ፡፡ የቅማንት ህዝብ ይዞት የተነሳዉ የመብት ጥያቄ ህገ-መንግስታዊ ከመሆኑ አንፃር በእየደረጃዉ የሚገኘዉ አስተባባሪ ኮሚቴ በህዝብ ዉክልና ሲንቀሳቀስ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ለማፍረስ ሳይሆን ይበልጥ እንዲጠናከር ለማድረግ መሆኑ ተዘነጋ፡፡ በእየደረጃዉ የሚገኝ የመንግስት አመራርም ሆነ የቅማንት ህዝብ የማንነትና ራስ አስተዳደር ህገ-መንግስታዊ ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ በመርህ ደረጃ የዓላማ ልዩነት እንደሌላቸዉ ተረሳ፡፡ ልዩነት ካላቸዉም ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በተግባር ከማክበር አንፃር ከግንዛቤ እጦት የመነጨ ወይም ስልጣንን ሽፋን በማድረግ ሌላ የተቃዋሚ ተልዕኮ ለማራመድ ከመሻት የመነጨ የአፈፃፀም ልዩነት ሊኖራቸዉ እንደሚችል ችላ ተባለ፡፡ ይህንን እዉነታ በመረዳት የፌዴራል መንግስቱ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የአማራ ክልል መንግስት ከፍተኛ አመራሮች የቅማንትን የማንነትና ራስ አስተዳደር ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ ህጋዊነት አረጋግጠዉ ጥያቄዉ ህዝብን ያረካ የመጨረሻ ምላሽ እስከሚሰጠዉ ድረስ በእየደረጃዉ ከሚገኙ የመንግስት አመራሮች ጋር ለቆሙለት የጋራ ዓላማ እንዲታገሉ ካሁን ቀደም በተደረጉ የስብሰባ መድረኮች አቋማቸዉን ደጋግመዉ ገልፀዋል፡፡ ይሁን እንጂ አምስቱን የመፍትሄ ሃሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ በተደረገበት ወቅት የተፈጠረዉ ዋናዉ ችግር አስተባባሪ ኮሚቴዉን ዛሬም እንደትናንቱ ያልሆነ ቅጥያ በመስጠት፤ ፀረ-ሠላም ኃይል እንደሆነ ያለአግባብ በመፈረጅ ፀረ-ህገመንግስታዊ አቋም እንዳለዉ በመስበክ ከህዝብ የመነጠል ስራ መሰራት እንዳለበት በፅሁፍ አስደግፎ ከዞን እስከ ወረዳ ያለዉ አመራር ወደ ህዝብ መዉረደ፡፡ ከዛሬ ጀምሮ ኮሚቴዉ ያለቀለት በመሆኑ አርፎ ይቀመጥ ካልሆነ ግን ህጋዊ እርምጃ ይወሰድበታል የሚሉ የማስፈራሪያ ንግግሮች ሲሰነዘሩ ህዝባዊ ቅሬታ እየፈጠሩ ያልተገቡ ጭቅጭቆችና ንትርኮች አስከተሉ፡፡ ይህም ሁኔታ በራሱ ሲታይ አምስቱን የመፍትሄ ሃሳቦች ህዝብን ባረካ መንገድ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ አስተባባሪ ኮሚቴዉ የመንግስት አጋዥ በመሆን የራሱን ትልቅ ድርሻ መወጣት የሚችል ሆኖ ሳለ ኮሚቴዉን አግልሎ ህዝብን ያላረካ ምላሽ ለመስጠት ተሞከረ፡፡
በመጨረሻም የክልሉ መንግስት በቅማንት ህዝብ የራስ አስተዳደር ጥያቄ ከተጠየቀባቸዉ 126-128 ቀበሌዎች መካከል 42ቱን ቀበሌዎች ብቻ ያካተተ የራስ አስተዳደር መልሻለሁ ብሎት አረፈ፡፡ ህዝቡም እንደስምምነቱ ሳይረካ ቀረ ብቻ ሳይሆን የክልሉ መንግስት ትልቅ የማታለል ሴራ እንደፈፀመበት ቆጠረዉ፡፡ የቅማንት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴም የክልሉ መንግስት በሰጠዉ ዉሳኔ ስላልረካ የፌዴሬሽን ም/ቤት በቀረበለት ይግባኝ መሠረት ጉዳዩን አይቶ የማያዳግም ዉሳኔ እንዲሰጥ አቤቱታ አቀረበ፡፡ አምስተኛዉ አገራዊ ምርጫ ተካሄደ፡፡ የቅማንት ህዝብም ህገ-መንግስታዊ መብቴን ያስከብርልኛል ብሎ ያመነበትን የፖለቲካ ፓርቲ “ብአዴን/ኢህአዴግ” መረጠ፡፡ በመንግስት አመራሮች በኩልም የምስጋና መልዕክት ለአስተባባሪ ኮሚቴዉ ተላለፈ፡፡ የምርጫ ዉጤት ይፋ ባልተደረገበት ወቅት የክልሉ መንግስት አፋጥኖ የቅማንትን የራስ አስተዳደር በ42 ቀበሌ ብቻ ለማቋቋም ተጣደፈ፡፡ የቅማንት ህዝብና ተወካዮችም የፌዴሬሽን ም/ቤት በይግባኝ የያዘዉን ጉዳይ ምላሽ ሳይሰጥ እና ይህን ቅማንትን ከሁለት የከፈለ የራስ አስተዳደር እንዳይቋቋም ቅሬታቸዉን በሰላማዊ መንገድ ለመግለፅ በጭልጋ ወረዳ አይከል ከተማ የሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄ ለሰ/ጎንደር ዞን አስተዳደር አቀረቡ፡፡ የሰ/ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ አቶ ግዛት አብዩ አዋጅ ቁጥር 3/1983 ከሚደነግገዉ ዉጭ ሰልፍ ማካሄድ እንደማይፈቀድና የቅማንት አስተባባሪ ኮሚቴም ህገ-ወጥ ቡድን በመሆኑ መፍረሱን በደብዳቤ አወጁ፡፡ የቅማንት አስተባባሪ ኮሚቴም ሰላማዊ ሰልፍ ይካሄድ አይካሄድ በሚለዉ ጉዳይ ላይ ለሶስት(3) ቀናት ያህል በአንክሮ መከረ፡፡ አሳማኝ ምክኒያቶች ቀርበዉ ሰላማዊ ሰልፉ እንዳይካሄድ ተወሰነ፡፡ የጭልጋ ህዝብ ስሜትም ገነፈለ፡፡ ወጣቱ ቁጣዉን ገለፀ፡፡የቅማንት አስተባባሪ ኮሚቴም ሰልፉ እሁድ ሊካሄድ በዋዜማዉ ቅዳሜ ዕለት በአይከል ከተማ ተገኝቶ ሰልፉ የማይካሄድበትን ምክኒያት ህዝቡንና ወጣቱን በማስረዳት ላይ እያለ በክልሉ መንግስት ልዩ ኃይል የተቀነባበረ ሴራ ግጭት እንዲነሳ ተደረገ፡፡ በርካታ ሰዎች ባደባባይ ገቢያ ላይ ተገደሉ፤ቆሰሉ፤ ተደበደቡ፤ቤታቸዉ ተደፈረ፤ ንብረታቸዉ ተዘረፈ፤ህጋዊ መሳሪያቸዉን ተቀሙ፤ህይወታቸዉን ለማትረፍ ሲሉ ጫካ ገቡ፤ከቤታቸዉ ተፈናቀሉ፤ ከስራ ተባረሩ፤ ታሰሩ፤ ወዘተ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የፌዴሬሽን ም/ቤት በቅማንት ጉዳይ ላይ ዉሳኔ አሳረፈ፡፡ አዋጅ ቁጥር 251/1993 አንቀፅ 53 (1) (2) በሚደነግገዉ መሠረት ይህ ዉሳኔ የመጨረሻና የሚመለከታቸዉ ወገኖች የማክበርና የማስፈፀም ግዴታ አላቸዉ፡፡ የፌዴሬሽን ም/ቤት በሰጠዉ ዉሳኔ ዉስጥ የሚከተሉት አራት (4) አንኳር የዉሳኔ አካሎች ተቀምጠዋል፤
1. በቋሚ ኮሚቴዉ የቀረበዉ የዉሳኔ ሀሳብና የክልሉ መንግስት የሰጠዉ ዉሳኔ ተመሳሳይ ሆነዉ በመገኘታቸዉ የክልሉ ምክር ቤት ለቅማንት ማህበረሰብ በሕገመንግስቱ በተቀመጡት መስፈርቶች መሠረት የሰጠዉን የማንነት እዉቅናና የራስ አስተዳደር ም/ቤቱ ተቀብሎ አፅድቆታል፣
2. በማህበረሰቡ አስተባባሪ ኮሚቴ በኩል የራስ አስተዳደሩን አከላለል በተመለከተ የቀረበዉን ቅሬታ በተመለከተ የክልሉ ም/ቤት ዋናዉን ጥያቄ ለመመለስ በሄደበት አግባብ እንዲፈታዉ ወስኗል፣
3. የሚመለከታቸዉ የክልሉ የተለያዩ የመንግስት አካላትም (ፍርድ ቤቶች፣ ምክር ቤቶችና አስፈፃሚ አካላት) የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ያሳለፋቸዉን የመጨረሻ ዉሳኔ እንዲፈፅሙና እንዲያስፈፅሙ፣የማህበረሰቡ አስተባባሪ ኮሚቴም ከክልሉ መንግስት ጋር ተቀራርቦ በመስራት የም/ቤቱን ዉሳኔ በመፈፀምና በማስፈፀም የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ፣
4. የሚመለከታቸዉ የም/ቤቱ ቋሚ ኮሚቴና ጽ/ቤቱም የዉሳኔዉን አፈፃፀም በተመለከተ ተገቢዉን ክትትል እንዲያደርጉ ወስኗል፡፡
የፌዴሬሽን ም/ቤት ዉሳኔ በመሠረቱ የፖለቲካና የህግ ዉሳኔ ነዉ፡፡ ልሙጥ የፍርድ ቤት ዉሳኔ አይደለም፡፡ የክልሉ ም/ቤት በድጋሜ የቅማንትን ጉዳይ ተመለከተ፡፡ ነገር ግን የፌዴሬሽን ም/ቤት በሰጠዉ ዉሳኔ አግባብና አንዳንድ የክልሉ ም/ቤት አባላት ባቀረቡት አስተያየት መሠረት ሳይሆን ቀደም ሲል በተወሰነዉ መንፈስ 42ቱን ቀበሌዎች ብቻ ያካተተ የራስ አስተዳደር የሚያቋቁመዉን አዋጅ ይዞ ቀረበ፡፡ የአማራ ክልል መንግስት የማንነቱንና የራስ አስተዳደር ጥያቄዉን በመርህ ደረጃ መመለሱ የሚመሰገን ሆኖ ሳለ በተግባር ግን የራስ አስተዳደሩን ሸራርፎ በ42 ቀበሌዎች ብቻ ለማቋቋም መፈለጉና ይህ ሁኔታ የቅማንትን ህዝብ የወደፊት የመልካም አስተዳደር ችግር የሚያባብስ መሆኑ ሲታይ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ ፈጠረ፡፡ ህዝቡ የራስ አስተዳደሩ በ42ቱ ቀበሌዎች ብቻ መዋቀሩን እንደማይቀበል ገለፀ፡፡ ሲቀጥልም በግፍ ያለምንም ምክኒያት ባደባባይ በልጆቻችን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል (genocide) የፈፀሙ የክልል መንግስት ባለስልጣናት ለፍርድ ሳይቀርቡልን፤ ያለአግባብ ታስረዉ እየማቀቁ ያሉ ልጆቻችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ካልተፈቱልን፤ ህይወታቸዉን ለማዳን ሲሉ ጫካ ገብተዉ እየተሰቃዩ ያሉ ልጆቻችን በሠላም ዋስትና ተሰጥቷቸዉ ወደ ቤታቸዉ እስካልተመለሱ ድረስ ሠላማዊ ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥልበታለን የሚል አቋም ይዟል፡፡ ተማሪዎችም ከቅማንት ህዝብ አብራክ የወጡ እንደመሆናቸዉ መጠን በህዝባቸዉ ላይ እየደረሰ ያለዉን ግፍና አፈና እያዩ መማር ስላቃታቸዉ ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ቅድመ ሁኔታዎች አፋጣኝ ምላሽ እስካልተሰጣቸዉ ድረስ ለአንድ ዓመት ያህል ትምህርት እንደሚዘጉና ሰላማዊ ትግላቸዉን እንደሚቀጥሉ በራሳቸዉ ጊዜ ዉሳኔ አሳልፈዋል፡፡ ተማሪዎችም ሰላማዊ አመፃቸዉን ከጀመሩ እንሆ ዛሬ ስድስተኛ (6ኛ) ቀናቸዉን ይዘዋል፡፡ ይሁን እንጂ በክልሉ መንግስት ልዩ ኃይል አማካኝነት በሠላማዊ መንገድ በሚታገሉ ተማሪዎች ላይ ጅምላ እስራት፣ ድብደባና ማሳደድ ተግባር እየተፈፀመባቸዉ ነዉ፡፡ በአጠቃላይ ሰ/ጎንደር በዚህ ወቅት የሠላም መደፍረስ ድባብ በከፍተኛ ደረጃ ይታይባታል፡፡ በሰላም ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀዉ የቅማንት የራስ አስተዳደር ጥያቄ ወደየት እያመራ ነዉ? ከክልሉ መንግስት ምን ይጠበቃል? ከፌዴራል መንግስትስ ምን ይጠበቃል? ከቅማንት ህዝብና ወኪሎቹስ? ከሌላዉ ህዝብስ ምን ይጠበቃል? በሚሉት ዙሪያ ላይ ሃሳቦችን እያነሳን እንወያይባቸዉ፡፡ ቸር ይግጠመን፡፡ ክፍል ሁለት ይቀጥላል፡፡

Advertisements
This entry was posted in Agaw Kemant. Bookmark the permalink.

One Response to Genocide Continues against Kemant People in Ethiopia, North Gondar to Stop Constitutional Demand for Self-Rule

  1. Tom karuawl says:

    You are talking about genocide a serious crime against humanity, but writing in a secretive language. How many people know this secretive language you have written your article?

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s