‘Legitimacy’ of ANRS Council’s Decision on Kemant’s Quest for Recognition and Self-Rule

በቅማንት ብሔረሰብ የማንነትና ራስ አስተዳደር ጥያቄ ላይ የአብክመ ምክር ቤት የሰጠዉ ዉሳኔ ህጋዊነት
by Tilahun Jember

1. መግቢያ

በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት ብሔር ብሔረሰቦች መካከል አንዱ የቅማንት ብሔረሰብ ሲሆን ህዝቡም በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በሰሜን ጎንደር ዞን በጎንደር ከተማ፣ በጎንደር ዙሪያ፣በላይ አርማጭሆ፣ በወገራ፣ በጭልጋ፣ በመተማ፣ በቋራ እና ደንቢያ ወረዳዎች በሙሉና በከፊል በተያያዘ መልክዓ ምድር ሰፍሮ የሚገኝ ነው፡፡

ባሁኑ ወቅት የቅማንት ህዝብ በትክክል ቢቆጠር ከአንድ ሚሊዮን በላይ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ ከዚህ በፊት በተደረጉት አገር አቀፍ የህዝብና ቤት ቆጠራዎችም የራሱ መለያ ኮድ ተሰጥቶት ሲቆጠር መኖሩን የመንግስት ሰነዶች ያረጋግጣሉ፡፡ የቅማንት ህዝብ በማንነቱና የማንነቱ መገለጫ በሆኑት ቋንቋዉ፣ ባህሉና ሃይማኖቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ ረገጣና ጭቆና በአንፃራዊነት በተደረገበት በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት እንኳ ሳይቀር እንደአንድ የተለየ ህዝብ ሲቆጠር የቆዬ ነዉ፡፡ በደርግ ዘመነ መንግስት ማለትም በ1976 ዓ.ም በተደረገዉ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ 169,169 ህዝብ ቅማንት ነኝ ብሎ የተመዘገበ ሲሆን ከዚህ ዉስጥ ደግሞ 166,973 ህዝብ ቅማንትኛ ቋንቋን እንደአፍ መፍቻ ቋንቋ ይናገርበት እንደነበር የህዝብ ቆጠራ ሰነዶች ይመሰክራሉ፡፡ ከኢትዮጵያም በህዝብ ቁጥር ደረጃም 17ኛ ደረጃ ላይ የነበር ህዝብ ነዉ፡፡

ወታደራዊዉ የደርግ መንግስት ስልጣን ላይ በወጣ ማግስትም የቅማንትን የብሔረሰብነት ማንነት ልክ እንደሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እዉቅና ሰጥቶ በአማራና በቅማንት መካከል የነበሩትን አድሎአዊና ጨቋኝ ግንኙነቶች በህግም ባይሆን በተግባር ለማረም ሙከራዎችን አድርጓል፡፡ ይሁን እንጂ የደርግ መንግስት የቅማንትን ማንነት ባደባባይ ባይክድም በሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ላይ ከፈፀመዉ ኢ-ዲሞክራሲያዊ የአገዛዝ በደል የባሰ በሚባል ሁኔታ በብሔረሰቡ ተወላጆች ላይ ከባድ የህይወት መስዋት አድርሷል፡፡ በጎንደር ከተማ ባደባባይ ላይ ከተጨፈጨፉትና በግፍ እየተገደሉ አስከሬናቸዉ በሊማሊሞ ገደል ከተወረወሩት ዉስጥ የቅማንቶች ቁጥር እጅግ ይበዛ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

ይህን ፅልመታዊ የደርግ አገዛዝ ከስሩ ለመገርሰስም የብሔረሰቡ ተወላጆች ቀድመዉ ከተቋቋሙ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመሰለፍ ይህ ነዉ የማይባል መስዋት ከፍለዋል፡፡ የደርግ አስከፊ የጭቆና ስርዓት በሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ትግል ከተወገደ በኋላ ይህን ተከትሎ በተቋቋመዉ ዴሞክራሲያዊና ፌዴራላዊ የመንግስት ስርዓት ተጠቃሚ እንደሚሆን የቅማንት ብሄረሰብ ተስፋዉ ከፍተኛ ነበር፡፡ የቅማንት ብሔረሰብ እንደማንኛዉም ብሔር ብሔረሰብ ማንነቱ በግልፅ ታዉቆ ራሱን በራሱ እያስተዳደረ የማንነቱ መገለጫ የሆኑትን ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ መጠበቅና ማሳደግ እንዲሁም አካባቢዉን በማልማት ካለበት የድህነት አረንቋ መዉጣት ይፈልግ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህን ተስፋዎችና መሠረታዊ ፍላጎቶች ብሄራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድሮችን ለማቋቋም የወጣዉ አዋጅ ቁጥር 7/1984 አጨለማቸዉ፡፡ ይህ አዋጅ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መስተዳድር (ክልል ሦስት) ዉስጥ አራት ብሔረሰቦች ብቻ ማለትም 1ኛ. አማራ 2ኛ. አገዉ-ካሚርኛ 3ኛ. አገዉ-አወንግኛ 4ኛ. ኦሮሞ (ቃሉ አካባቢ) መኖራቸዉን እዉቅና ሲሰጥ የአገዉ ህዝቦች አንዱ አካል የሆነዉን የቅማንት ብሔረሰብ ግን ያለምንም ምክኒያት በዝምታ አልፎታል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በ1987 ዓ.ም በተደረገዉ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ የቅማንት ህዝብ የራሱ መለያ ኮድ ተሰጥቶት በቅማንት ማንነቱ ተቆጥሯል፡፡ በተደረገዉ የቆጠራ ዉጤትም 172,291 ህዝብ ቅማንት ብሎ የተመዘገበ ሲሆን (this figure is about 20% of the actual present Kemant population) ከዚህ ዉስጥ 5,075 ህዝብ ደግሞ ቅማንትኛ ቋንቋን በአፍ መፍቻና ሁለተኛ ቋንቋነት ይጠቀሙበት እንደነበር ነዉ፡፡ ከኢትዮጵያ በህዝብ ቁጥር ደረጃም 10ኛ ደረጃ ላይ ነበር፡፡

አዋጅ ቁጥር 7/1984 የፈጠረዉን ቅሬታ ተከትሎም የቅማንት ብሔረሰብ ህገ-መንግስታዊ የመብት ጥያቄ በተቆርቋሪ ወገኖች አነሳሽነት ተጀመረ፡፡ በወቅቱ ጥያቄውን ያነሱ ግለሰቦች እንቅስቃሴያቸዉን በማህበርና በኮሚቴ መልክ የጀመሩ ሲሆን ከወገናቸው ሰፊ ድጋፍና ከመንግስት ሰሚ ባያገኙም በቅማንት ብሔረሰብ ታሪክ፣ ባህልና ቋንቋ ዙሪያ እውቀታቸውን፣ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን በማፍሰስ እስከ 1999 ዓ.ም ድረስ ጥያቄውን ህያው አድርገው አቆይተውታል፡፡ ህዳር 29 ቀን 1999 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ በተካሄደዉ የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ቀን የብሔረሰቡ ተወካዮች እንዲሳተፉ ፌዴሬሽን ም/ቤት ጋብዟቸዉ 3 ተወካዮች ሄደዉ ተሳትፈዉ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከዚያ ቀን ወዲህ በባዓሉ ቀን እንዳይሳተፉ በይፋ ተከልክለዋል፡፡ በ1999 ዓ.ም የተደረገዉ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ከላይ የተጠቀሰዉን አዋጅ ፈለግ በመከተል የቅማንትን ማንነት በድጋሜ ሰርዞ ቀረበ፡፡ ይህን ተከትሎም የብሔረሰቡ ተወካዮች በወቅቱ፡-
1ኛ) ለሰሜን ጎንደር ዞን ስታትስቲክስ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት፣
2ኛ) ለክልሉ መንግስት ህዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን እና
3ኛ) ለፌዴራል መንግስት ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የቅማንት ህዝብ እንደ ድሮዉ የቆጠራ ኮድ ተሰጥቶት እንዲቆጠር በ01/09/99 ጠይቀዉ ነበር፡፡ እንዲሁም በ08/9/99 ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄዉ ቀርቦ ማስተካከያ ሳይደረግ ቆጠራዉ ተጠናቋል፡፡ በመንግስት በኩል በተቋም ደረጃ የተካሄደ ከጥንት ጀምሮ የነበረን የህዝብ ማንነት ማጥፋት ድርጊት ቢሆንም ለዚህ ታሪካዊ ስህተት አዘል ድርጊት ግን ኃላፊነት የሚወስድ አንድም የመንግስት አካል አልተገኘም፡፡ የ1999 ዓ.ም የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ዉጤት ይፋ ከሆነ በኋላ ቅማንት እንደብሔረሰብ አለመቆጠሩ ሲታወቅ የማንነት ጥያቄው የህዝቡን ከፍተኛ ድጋፍ አግኝቶ ተጠናክሮ ቀጠለ፡፡ ለአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ጥያቄዉን በተመለከተ የጥናት ዉጤት (survey study) በ30/12/1999 ዓ.ም በወቅቱ ጥያቄዉን ሲያንቀሳቅሱ በነበሩ የብሔረሰቡ ተወካዮች ቀርቧል፡፡ ጥያቄዉ ለክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ በ14/9/2000 ዓ.ም ቀርቦ ነበር፡፡ በተመሳሳይ መንገድ በ11/06/2001 ዓ.ም የቅማንት ብሔረሰብ ማንነቱ እንዲከበር እና የራሱን አስተዳደር በራሱ የመወሰን መብቱ እንዲከበር ለፌዴሬሽን ም/ቤት ጥያቄዉ ቀርቧል፡፡

ቅማንት በስሙ አለመቆጠሩና ማንነቱ አለመከበሩ የብሔረሰቡ ተወላጅ የሆነዉን ሁሉ ከዳር እስከዳር የቀሰቀሰና የኢትዮጵያዊነት ዜግነቱን እንዲሁም የቅማንትነት ህልውናውን የገፈፈ ስሜት ፈጠረ፡፡ ህዝቡም ከዘር ማጥፋት (silent identity genocide) የማይተናነስ ወንጀል እንደተፈፀመበት አድርጎ አየው፡፡ በኋላም የብሔረሰቡ ተወላጆች አዋጅ ቁጥር 251/2001 አንቀፅ 21(2) በሚደነግገዉ መሠረት የቀረበዉን ህገ-መንግስታዊ ጥያቄ ህጋዊነቱን ጠብቆ በተደራጀ መንገድ የሚመራ 120 አባላት የያዘ ምክር ቤት ግንቦት 16 ቀን 2001 ዓ.ም አቋቋሙ፡፡ ምክር ቤቱም የእለት ከእለት እንቅስቃሴዉን የሚመራ የዞን አስተባባሪ ኮሚቴ ግንቦት 30 ቀን 2001 ዓ.ም ሰየመ፡፡ አስተባባሪ ኮሚቴዉም የራሱን አደረጃጀት ፈጥሮ የብሔረሰቡን የመብት ጥያቄ በተወካይነት በዴሞክራሲያዊና በህጋዊ መንገድ በመምራት በርካታ ስራዎችን አከናዉኗል፡፡ አዋጅ ቁጥር 251/2001 በሚደነግገዉ መሠረት ጥያቄዉን ለክልሉ መንግስትና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ሃምሌ 15 ቀን 2001 ዓ.ም አቅርቧል፡፡ ለክልሉ መንግስትና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄዉ በዚሁም ቀን ሲቀርብ የ18,584 (አስራ ስምንት ሺ አምስት መቶ ሰማኒያ አራት) ህዝብ ስም፣ ቀበሌና ፊርማ እንዲሁም የአንድ ወረዳና የአስር ቀበሌ አስተዳደሮች የአስተያየት ማስረጃ አያይዞ አቅርቧል፡፡

የፌዴሬሽን ም/ቤት የጊዜ ገደብ አስቀምጦ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ስልጣኑን በመጠቀም ለቀረበዉ የመብት ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጥ መመሪያ ከሰጠበት ጊዜ አንስቶ ከክልሉ መንግስት ጋር ከጥያቄዉ ጋር በተያያዘ አስተባባሪ ኮሚቴዉ በርካታ ግንኙነቶችን አድርጓል፡፡ የቅማንት ብሔረሰብ የማንነትና ራስ አስተዳደር የመብት ጥያቄ ህገ-መንግስታዊ መሆኑን ለሚመለከተዉ አካል ሁሉ (በእየደረጃዉ የሚገኙትን የመንግስት ባለስልጣኖች ጨምሮ) በደብዳቤም ሆነ በአካል በመገኘት አስረድቷል፤ ድጋፍም ጠይቋል፡፡ የብሔረሰቡን ፍላጎት በማድመጥና በመከተል የተነሳዉ ህገ-መንግስታዊ የመብት ጥያቄ አቅጣጫዉን እንዳይስትና የህግ የበላይነት ግንዛቤ እንዲፈጠር ለማድረግ

ሁሉም ሰዉ ተሳትፎ ያደረገባቸዉ በርካታ ህዝባዊ ስብሰባዎች፣ የምክክር መድረኮችና አዉደ ጥናቶች እንዲካሄዱ አድርጓል፡፡ ለአብነት ለመጥቀስ ያህል ሚያዝያ 29 ቀን 2003 ዓ.ም በቅማንት ብሔረሰብ ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ ዙሪያ ከፍተኛ ሙሁራን (ፕ/ር ላጲሶ ጌ ዴልቦን ጨምሮ) የተሳተፉበትና የመሩት አዉደ ጥናት አካሂዷል፡፡ በዚህ ወቅት ከፍተኛ ባለስልጣናት ከታች እስከ ላይ እንዲገኙ ጋብዟል፡፡ የመንግስት መገናኛ ብዙኃን ትዕይንቱን እንዲዘግቡና እንዲያሰራጩ በተመሳሳይ መንገድ አስተባባሪ ኮሚቴዉ ጋብዟቸዉ ነበር፡፡ በቅማንት ህዝብ ላይ የሚደርሰዉን የመልካም አስተዳደር ችግር መንግስት እንዲያስቆምና መፍትሔ እንዲሽት በተደጋጋሚ ከክልል እስከ ፌዴራል ድረስ ለሚገኙ የመንግስት ባለስልጣናት በደብዳቤም ሆነ በአካል ቀርቦ አስረድቷል፤አሳስቧል፡፡

በጥር ወር 2003 ዓ.ም የክልሉ መንግስት የቀረበዉን ጥያቄ በጥናት ለመመለስ የመጀመሪያዉን የዳሰሳ ጥናት ለማካሄድ በተንቀሳቀሰበት ወቅት ጥናቱ ግልፅና ገለልተኛ በሆነ መንገድ እንዳልተካሄደ በመገንዘብ ይህንን ጉዳይ አስተባበሪ ኮሚቴዉ የካቲት 01 ቀን 2003 ዓ.ም በደብዳቤ ለፌደሬሽንና ለክልሉ መስተዳድር አሳዉቋል፡፡ ታህሳስ 25 ቀን 2004 ዓ.ም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና ሌሎች ባለስልጣናት በተገኙበት የመጀመሪያዉ የጥናት ዳሰሳ ዉጤት በተገመገመበት ወቅት ጥናቱ ችግር እንዳለበት በመተቸት የብሔረሰቡ ተወካዮች የሚሳተፉበት የጋራ የጥናት ቡድን ተቋቁሞ ጥናቱ በማያዳግም መልኩ እንደገና እንዲጠና አስተባባሪ ኮሚቴዉ አሳስቧል፡፡

በዚሁም መሠረት መጋቢት ወር 2004 ዓ.ም የክልሉ መንግስት ለሁለተኛ ጊዜ ባቋቋመዉ የጥናት ቡድን ዉስጥ አራት አባላት ከቅማንት በኩል እንዲሳተፉ አድርጓል፡፡ ሚያዝያ 04 ቀን 2004 ዓ.ም አስተባባሪ ኮሚቴዉ ጥናቱ በአግባቡና በሠላም እንዲካሄድ አስፈላጊዉን ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግ አስቀድሞ በደብዳቤ የገለፀ ቢሆንም የጥናቱ አንድ ሶስተኛ እንደተጠናቀቀ በመንግስት ተወካዮች ምክኒያት የተቋረጠ መሆኑን አረጋግጦና በማስረጃ አስደግፎ ጉዳዩን በአካል በመቅረብ ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስረድቷል፡፡

በመቀጠልም ግንቦት 22 ቀን 2004 ዓ.ም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ አያሌው ጎበዜ፣ ክቡር አቶ በረከት ስምዖን፣ ሌሎች የክልሉ ባለስልጣናትና የብሔረሰቡ ተወካዮች በተገኙበት በተደረገዉ ዉይይት ከዚህ በኋላ ጥናት እንደማያስፈልግና ባለዉ ማስረጃ መሠረት ዉሳኔ እንዲሠጥ ይህ የሚታለፍ ከሆነ ደግሞ ገልተኛ በሆነ አካል (ለምሳሌ ደቡብ ዩኒቨርስቲ) ጥናቱ እንዲጠና አስተያየት አቅርቧል፡፡ በተደረሰዉ ስምምነት መሠረትም አስተባባሪ ኮሚቴዉ የጥናት ሃሳብ (Research Proposal) በማዘጋጀትና ጥናቱን ለማካሄድ የሚያስፈልገዉን ወጭ በመጥቀስ ለክልሉ መንግስት ሃምሌ 04 ቀን 2004 ዓ.ም አቅርቧል፡፡ ሆኖም የክልሉ መንግስት የቀረበዉን የጥናት ሃሳብ ከተመለከተ በኋላ ቀደም ሲል ከተደረሰዉ ስምምነት ባፈነገጠ መልኩ ጥልቅ ጥናት እንደማያስፈልግ በመግለፅ በመልካዓ ምድርና በቋንቋ ዙሪያ ብቻ አስተባባሪ ኮሚቴዉ በእጁ ላይ

የሚገኘዉን ማስረጃ ይዞ እንዲቀርብ ቀጭን ትዕዛዝ በማስተላለፉ ምክኒያት አስተባባሪ ኮሚቴዉ በራሱ ወጭና ጉልበት አጥንቶ ያቀረበዉን ጥናት ጥቅምት 11 ቀን 2005 ዓ.ም ክቡር አቶ በረከት ስምኦን፣ ክቡር አቶ አያሌዉ ጎበዜ፣ ሌሎች የክልሉ ባለስልጣናት እና የብሔረሰቡ ተወካዮች በተገኙበት አቅርቧል፡፡ ባቀረበዉ ጥናትም የቅማንት ብሔረሰብ በፌዴራሉ ህገ-መንግስት አንቀፅ 39(5) ስርም ሆነ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ህገ-መንግስት አንቀፅ 39(7) ስር የተቀመጡትን የብሔረሰብነት መስፈርቶች አሟልቶ እንደሚገኝ በማስረጃ አስደግፎ አቅርቧል፡፡ የቅማንት ብሔረሰብ የማንነትና ራስ አስተዳደር ጥያቄም እንዲፈቀድ መንግስትን በአንክሮ ጠይቋል፡፡

የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ለአራተኛ ጊዜ ብቻዉን ያጠናዉን ጥናት ሰኔ 25 ቀን 2005 ዓ.ም በክልሉ ካቢኔዎች ፊት ባቀረበበት ወቅትም በተመሳሳይ መንገድ አስተባባሪ ኮሚቴዉ የክልሉ መንግስት የቀረበዉን የማንነትና ራስ አስተዳደር ጥያቄ በሃቅ ላይ ተመስርቶ እንዲመልስ አጠንክሮ አሳስቧል፤ለምኗል፡፡

2. የነበሩና ተጠናክረዉ የቀጠሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች

የቅማንት ብሔረሰብ ባለፉት የፖለቲካ ስርዓቶች ግፍና ጭቆና ከፍተኛ በደል ሲደርስበት የነበረ ነዉ፡፡ በኢኮኖሚ፣በማህበራዊ፣ በባህላዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ሁሉ እኩል ከአማራዉ ህዝብ ጋር ተጠቃሚ እንዳይሆን ከጥንት ጀምሮ የነበረዉ የተለየ የቅማንት ማንነቱና የማንነቱ መገለጫዎች በሌሎች እይታና የተሳሳተ ግንዛቤ ትልቅ መሰናክል ፈጥረዉበት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለሚከሰቱ አድሏዊ የአስተዳደር በደሎች (direct or indirect discrimination) ሰለባ ሆኖ ቆይቷል፡፡ የቅማንት ህዝብ ከሰብኣዊነት ፍጡር ወጥቶ ከጥንት አንስቶ እንደ እፅና እንስሳ መፈረጁና መታየቱ የጭቆናዎች ሁሉ ቁንጮ ያደርገዋል፡፡ ቅማንቶች ወይራ ከሚባል ዛፍ የተፈጠሩ ናቸዉ የሚለዉ ኢ-ሳይንሳዊ አባባል በአማራዉም ሆነ በሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ስር የሰደደ አስተሳሰብ ነዉ፡፡ የቅማንቶች እናት ሰሳ የምትባል እንስሳ ነች፤ ቅማንቶች ልክ እንደእንስሳ ጅራት አላቸዉ የሚለዉም አስተሳሰብ እንዲሁ በህብረተሰቡ ዉስጥ ገንግኖ የቆዬ አስተሳሰብ ነዉ፡፡ የቅማንትኛ ቋንቋ እንዳያድግና እንዲጠፋ ያልተሰጠዉ አሉታዊ ስምና ያልተደረገ ድርጊት የለም ማለት ይቻላል፡፡ የቅማንትኛ ቋንቋ የወፍ ቋንቋ ነዉ፤የቅማንትኛ ቋንቋ ለቤተ መንግስትና ለቤተ ክህነት አይበቃም የሚሉትን መጥቀስ በቂ ነዉ፡፡ በቅማንት ህገ-ልቡና ሃይማኖትም ጭምር ተመሳሳይ አድቃቂና አግላይ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች በቅማንት ብሔረሰብ ዉስጥ የነበሩና የቀጠሉ ናቸዉ፡፡ እነዚህን ኢ–ሰብአዊ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች ደግሞ ከህብረተሰቡ አብራክ በወጡና ቅማንትን ያስተዳደሩ የመንግስት አስተዳዳሪዎች (በዋናነት የአማራ ገዥዎች) ሳይቀር በግልፅም ሆነ ግልፅ ባልሆነ መንገድ ሲንፀባረቁና ሲደገፉ የነበሩና ያሉ ናቸዉ፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ አሉታዊ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች በታሪክ ሰነዶች እና በሳይንሳዊ ጥናትና ምርምሮች ሳይቀር ተመዝግበዉ የሚገኙ ቢሆንም የእያንዳንዱን ቅማንት አንደበት ብቻ ማድመጥ በቂ ሊሆን ይችላል፡፡

ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ዓይነት አሉታዊ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች በቅማንት ህዝብ ኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊ፣ባህላዊና ፖለቲካዊ ህይወት ላይ ከፍተኛ የሆነ ጋሬጣ ሰንቅሮበታል፡፡ ቅማንቶች ወደ ፖለቲካዉ መስክ እንዳይዘልቁ ከመቸ ወዲህ ነዉ ቅማንት ሰዉ ሁኖ ለስልጣን የሚበቃዉ የሚለዉ አባባል በገዥዎች በኩል ይሰነዘርባቸዋል፡፡ በተግባር ያለዉ ስርዓት ፈቅዶላቸዉ ሳይሆን በግላቸዉ ጥረት ተሳክቶላቸዉና ማንነታቸዉን ሳይቀር ደብቀዉ በጣት የሚቆጠሩ የቅማንት ተወላጆች ወደ ስልጣን የወጡ እንደሆን ህቡህ በሆነ መንገድ አንዳንዴም ግልፅ በሆነ መንገድ መጥፎ ቅጥያ የቀጠሉለትን የቅማንት ማንነት በማንሳት ያገሏቸዋል፤ያድሙባቸዋል፤ ከስልጣን ያወርዷቸዋል፡፡ ያለፈዉን ታሪካዊ የፖለቲካ በደል እንኳ ትተን ስለህዝቦች ማንነት ነፃነት በህገ-መንግስት በታወጀበት በአሁኑ የፖለቲካ ስርዓት ምን ያህል የቅማንት ልጆች በማንነታቸዉ ሳያፍሩና አንገታቸዉን ሳይደፉ በፖለቲካዉ ምህዋር ይሳተፋሉ የሚለዉን ጥያቄ ወስዶ ማየቱ የችግሩን ጥልቀት ለመረዳት ይረዳል፡፡ ማንም የኢህዴግ የፖለቲካ አመራር እንደሚረዳዉ የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነዉ ህገ-መንግስት ከሚደነግጋቸዉ መርሆችና መብቶች ትልቁን ድርሻ የሚወስደዉ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ልዑላዊነት ነዉ፡፡ የኢህዴግም ሆነ የብአዴን የፖለቲካ ፕሮግራምም ከመጠን በላይ የሚሰብከዉ ይህንኑ ነዉ፡፡ ይሁን እንጂ በእየደረጃዉ የሚገኙ የኢህአዴግ ወይም የብአዴን አባል የሆኑ የቅማንት ተወላጆች ስለቅማንት ብሔረሰብ ማንነት ባደባባይ ያለምንም ፍራቻና መሸማቀቅ በነፃነት መናገር ቀርቶ ድምፃቸዉን ያጠፉት ቅማንቶች እንኳ የአስተዳደር ግፍ ቀማሽ ከመሆን አላመለጡም፡፡ ይህ ሁኔታ በተለይ ደግሞ የቅማንት ብሔረሰብ የማንነትና ራስ አስተዳደር ጥያቄ ተጠናክሮ በቀጠለበት ባሁኑ ሰዓት ብሶበታል፡፡ የቅማንትን የማንነትና ራስ አስተዳደር ጥያቄ ትደግፋላቹህ በሚል ሰበብ ከስራቸዉ የሚፈናቀሉ፤ ከስራ እድገት ያላግባብ የሚታገዱ፤ ከስራ ደረጃ ያለአግባብ ዝቅ የሚደረጉ፤ ሩቅና አስቸጋሪ ወደ ሆኑ የስራ ቦታዎች ያለአግባብ የሚዘዋወሩ እና በፍትሃዊ የስራ ዉድድር ወሳኝ ወደ ሆኑ የመንግስት የስልጣን ቦታዎች እንዳይመጡ የሚደረጉት የቅማንት ልጆች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ከእነዚህ የፖለቲካ ችግሮች ለማምለጥ ሲባል የቅማንትነት ማንነታቸዉን ክደዉ አሁን እየተነሳ ያለዉን ህገ-መንግስታዊ የመብት ጥያቄ ማዉገዝ ወይም አለመደገፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህ አባባል ደግሞ በቂ ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል፡፡

በኢኮኖሚዉም ዘርፍ ችግሩ ተመሳሳይ ነዉ፡፡ የፖለቲካ ነፃነት የሌለዉ ህዝብ በመሠረቱ በልማትና በኢኮኖሚ ሊያድግና ሊበለፅግ አይችልም፡፡ የተቆርቋሪነት መንፈስ አንግቦ ህዝቡን በዲሞክራሲያዊ መንገድ አሳትፎ ልማትና የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት የፖለቲካ ነፃነት በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡ ከአድሎ የፀዳ መልካም አስተዳደር ያስፈልጋል፡፡ አለመታደል ሆኖ የቅማንት ህዝብ ከጥንት ጀምሮ የዚህ መሠረታዊ መብት ተቋዳሽ አልሆነም፡፡ የአካባቢዉ ገዢዎች የዚህን ህዝብ ጉልበትና ሃብት በዝብዞ ከመጠቀም ዉጭ እስካሁን ድረስ ምንም የፈየዱለት ነገር የለም፡፡ የመሠረታዊ ልማት ጉዳይ ጥያቄ ዉስጥ ከገባ ዉሎ አድሯል፡፡ ት/ቤቶች፣ መንገዶች፣ የንፁህ ዉሃ አቅርቦት እና ሌሎች መሠረታዊ የልማት አዉታሮች በአድሏዊና በምን ግዴለሽነት አስተዳደር ችግር ዉስጥ ወድቀዉ የፍትህ ያለህ እያሉ ይገኛሉ፡፡

በማንነታቸዉ ላይ የተፈጠሩት አሉታዊ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች በቅማንቶች ማህበራዊ ህይወት ላይ ያስከተሉት ችግርም በጣም የከፋ ነዉ፡፡ ከሰዉነት ማንነታቸዉ ላይ መጥፎ ታርጋ ተለጥፎባቸዉ ከሰብኣዊነት ተራ የወጡ ህዝቦች ሳያፍሩና ሳይሸማቀቁ ባደባባይ አብረዉ መሄድና ስለጉዳያቸዉ በጋራ ሊመክሩ አይችሉም፡፡ ቅማንቶች እንደማንኛዉም ነፃ ህዝብ በማንነታቸዉ ተጠራርተዉ ማህበራዊ ህይወታቸዉን በጋራ በግልፅ ለመምራት አይችሉም፤ ካደረጉም በሹክሹክታ ማንም እንዳይሰማቸዉ ሁነዉ ነዉ፡፡ የተወለዱበትን ቀዬ እንኳ ደፍሮ በግልፅነት ለመናገር አሁንም ድረስ ፈተናዉ ከባድ ነዉ፡፡ በቅማንቶች ማንነት ላይ የተቃጣዉ በደል እና ተፅዕኖ ባህላቸዉን፣ቋንቋቸዉን፣ታሪካቸዉንና ቀደምት ሃይማኖታቸዉን ባደባባይ በነፃነት እንዳይጠቀሙበት እና እንዳይንከባከቡት አድርጓቸዋል፡፡

ጠቅለል ባለ መልኩ ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ታሪካዊ የሆኑና ስር የሰደዱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በቅማንት ህዝብ ዘንድ አሁንም ድረስ ያሉ ሲሆን የቅማንት የማንነትና ራስ አስተዳደር ጥያቄ ከተነሳ ወዲህ በተጨባጭ በመንግስት አካላት በኩል የተወሰዱትን የመልካም አስተዳደር በደሎች ጥቂቶችን ለአብነት ወስዶ ማዬት ተገቢ ሊሆን ይችላል፤
1) ላይ አርማጭሆ ወረዳ በሚገኘዉ የቅማንት ህዝብ ላይ ምንም ዓይነት ህጋዊም ሆነ ነባራዊ ምክኒያት ሳይኖርና ሳይገኝ ለወረዳዉ ህዝብ የተመደበዉን በጀት ያላግባብ ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በመመደብ በህዝብ ላይ ሽብርና ፍርሃት እንዲፈጠር ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ የመከላከያ ሰራዊቱ ባሳየዉ ጨዋነት የከፋ ችግር ሳይፈጠር ከአንድ ሳምንት በኋላ አካባቢዉን ለቆ ሂዷል፡፡ ይህንን መረን የለቀቀ ህገ-ወጥ ድርጊት በፈፀመዉ በወረዳዉ አስተዳዳሪ ላይ የማስተካከያ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ህዝቡ ጩኸቱን ቢያሰማም በተቃራኒዉ በስልጣን ዕድገት ሸልመዉታል፤
2) መተማ ወረዳ በሚገኙ የቅማንት አርሶ አደር ባለሃብቶች ላይ ተመሳሳይ በደል ተፈፅሟል፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸዉ እነዚህ ባለሃብቶች የቅማንትን የማንነትና ራስ አስተዳደር ጥያቄ ይደግፋሉ በሚል ሰበብ የሻቢያ አሸባሪ ድርጅት ተላላኪዎች ናቸዉ በሚል ከዞን እስከ ወረዳ ባሉ የመንግስት ባለስልጣኖች የተቀነባበረ የዉሸት መረጃ መተማ አካባቢ ለሚገኘዉ የመከላከያ ሰራዊት የስም ዝርዝራቸዉ ተላልፎ ተሰጥቷል፡፡ ሆኖም የመከላከያ ሰራዊት አሁንም ባደረገዉ ማጣራትና ባሳየዉ ህዝባዊ ታማኝነት የቅንና ታታሪ አርሶ አደር ባለሃብቶች ህይወት ሊተርፍ ችሏል፤
3) መተማ ወረዳ የሚገኙ ቅማንት አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ቅማንት በመሆናቸዉ በግፍ እንዲገደሉ ተደርገዋል፤የመንግስት አመራሮች እጅ እንዳለበትም በቂ ማስረጃዎች ይገኛሉ፡፡ ምንም ዓይነት ህጋዊ ምክኒያት ሳይኖር በዚህ በመተማ አካባቢ የሚኖሩ የቅማንት አርብቶ አደሮች በኮንትሮባንድ ወንጀል ሰበብ መንጋ ከብቶቻቸዉን ባደባባይ እየተነጠቁ ለድህነት ተዳርገዋል፡፡ ከቀበሌ እስከ ክልል ድረስ ለሚገኙት የመንግስት አካላት ጩኸታቸዉን በማሰማት ለማስረዳት ቢሞክሩም ከባድ ፈተና ሁኖባቸዋል፤
4) ቀደም ሲል በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደዉ የናሙና ህዝብ ቆጠራ ወቅት የቅማንት ህዝብ በራሱ ስም ቅማንት ተብሎ እንዲቆጠር ጥያቄ ቢያቀርብም ጥያቄዉን ከምንም ባለመቁጠር ተገዶ አማራ ወይም ሌሎች በሚል እንዲቆጠር ተደርጓል፡፡ ይህም ታሪካዊ ስህተት ራሱን የደገመበት ወቅት ነዉ፤
5) የቅማንት ብሔረሰብ ልክ እንደሌሎች ህዝቦች ወግ ባህላቸዉን ይዘዉ ህዳር 29 ቀን በእየዓመቱ በሚከበረዉ የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ቀን እንዳይገኙ በይፋ በመንግስት ተከልክለዋል፤
6) የቅማንትን ጉዳይ በተመለከተ ማንኛዉም ዓይነት ሳይንሳዊ ጥናት ለማካሄድ የሚመጡ አጥኚዎች መረጃ ፈልገዉ ወደ ክልሉ መንግስት በሚሄዱበት ጊዜ መረጃ እንዳያገኙ ተደርገዋል ወይም እየተደረጉ ነዉ፤
7) የቅማንት ማንኛዉም ጉዳይ (አስተባባሪ ኮሚቴዉ የሚያደርጋቸዉ ስብሰባዎች፣ታሪካዊ ዘገባዎች፣ህዝቡን በተመለከተ የሚወጡ ሙዚቃዎች ወይም የኪነ-ጥበብ ዉጤቶች፣ ወዘተ) በመገናኛ ብዙኋን እንዳይለቀቁና ሽፋን እንዳያገኙ ታግደዋል፤የመገናኛ ብዙኃንም ዘገባቸዉን ከማሰራጨት ተቆጥበዋል፤
8) የቅማንትኛ ቋንቋ ትምህርት በመንግስት ትምህርት ቤቶች እንዳይሰጡ በወረዳ አስተዳዳሪዎች ተከልክለዋል፤
9) ህዝባዊ ስብሰባዎችን ለማካሄድ በሞንታርቦ (በድምፅ ማጉያ) በድምፅ ብክለት ሰበብ ህዝባዊ ጥሪ ለማድረግ እንደማንችል በዞኑ አስተዳዳሪ በኩል በይፋ ተከልክለናል፤ይሁን እንጂ በጎንደር ከተማ ዉስጥ በተፈለገዉ መንገድ የሞንታርቦ ቅስቀሳ ሲደረግ የሚወሰድ እርምጃ የለም፡፡ ይህም ደግሞ ግልፅ አድሎ መኖሩን ያሳያል፤
10) የቅማንት የማንነትና ራስ አስተዳደር ህገ-መንግስታዊ ጥያቄ የጥቂት ስልጣን ፈላጊ ግለሰቦች ብቻ ሳይሆን የመላዉ ቅማንት ህዝብ ጥያቄ መሆኑን በትዕይንተ ህዝብና ሰላማዊ ሰልፍ ለማሳየት ቢጠየቅም የሰ/ጎንደር ዞን አስተዳደር በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 30 ስር የተደነገገዉን መብት በሚፃረር መንገድ እና አዋጅ ቁጥር 3/1983 ከሚደነግገዉ መንፈስ ዉጭ ማንኛዉም ትዕይንተ ህዝብም ሆነ ሰላማዊ ሰልፍ እንዳይካሄድ በደብዳቤ አግዷል፤
11) የቅማንት ልማት ማህበር (ቅልማ) እንደማንኛዉም የልማት ድርጅት በፌዴራል ደረጃ ህጋዊ ዕዉቅና ያገኘ ቢሆንም የአማራ ልማት ማህበርን (አልማ) ለማፍረስ የመጣ ድርጅት ነዉ በሚል ዉዥምብር ባካባቢዉ ልማት እንዳይመጣ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነዉ፡፡

3. የአራቱ ጥናቶች ሂደት ዲሞክራሲያዊነትና ህጋዊነት

የቅማንት ብሔረሰብ የማንነትና ራስ አስተዳደር ጥያቄ ቀደም ብሎ በ1980ዎቹ የተጀመረ ቢሆንም ልክ እንደዛሬዉ አዋጅ ቁጥር 251/1993 በሚደነግገዉ መሠረት በተደራጀ መንገድ ከቀረበበት ከሃምሌ 15 ቀን 2001 ዓ.ም አንስቶ ሲሰላ ከአራት ዓመታት በላይ ሁኖታል፡፡ ይሁን እንጂ የቀረበዉ የማንነትና ራስ አስተዳደር ጥያቄ ከላይ በተጠቀሰዉ አዋጅ መሠረት በሁለት ዓመታት ዉስጥ ምላሽ ማግኘት ይገባዉ ነበር (አንቀፅ 20(3))፡፡ የአማራ ክልላዊ መንግስት ጥያቄዉ ከቀረበለት ጊዜ ጀምሮ ህጉ በሚፈቅደዉ የጊዜ ገደብ ዉስጥ ምላሽ ለመስጠት ፍላጎት አላሳየም፡፡ ጥያቄዉን በተወካይነት ይዘዉ የሚቀርቡትን የአስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ተገቢ ያልሆነ ዘለፋና በተነሳዉ ጥያቄ ዙሪያ ከፍተኛ ምሬት በማሰማት ግፋ ሲልም የጥቂት ስልጣን ፈላጊዎች ጥያቄ እንጂ የብዙኋኑ ህዝብ ጥያቄ እንዳልሆነ የሃሰት ወሬ በመንዛትና የተሳሳተ ግንዛቤ በህብረተሰቡም ሆነ በመንግስት በኩል እንዲፈጠር ለማድረግ ከላይ እስከ ታች በእየደረጃዉ ባሉ የመንግስት ባለስልጣኖች ያልተሰራ ስራ የለም፡፡

አስተባባሪ ኮሚቴዉም ጥያቄዉ የመላዉ ህዝብ መሆኑን በህጋዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ በማስረዳት ይህን የተሳሳተ ግንዛቤ ለማስቀየር ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፤እያደረገም ነዉ፡፡ ከጅምሩ ህዝባዊ ስብሰባዎችን ለማካሄድ ይቻል ዘንድ የህዝብ አዳራሾችን አስፈቅዶ ለመጠቀም የፈጀዉ ፈተና የቀረበዉን ጥያቄ በዲሞክራሲያዊና ህጋዊ መንገድ ለመፍታት በመንግስት ባለስልጣናት (በተለይም በወረዳና ዞን አመራር) በኩል ፍላጎት አለመኖሩን የሚያሳይ ነዉ፡፡ ቀጥሎም ህዝባዊ ስብሰባዎች በሚደረጉበት ወቅት ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተዉ ለሚያስተዳድሩት ህዝብ የሚገባዉን መልዕክት እንዲያስተላልፉና በቀረበዉ ህገ-መንግስታዊ ጥያቄ ዙሪያ ያላቸዉን አስተያየት እንዲሰጡ ህዝቡ በክብር ሲጋብዛቸዉና ሲጠራቸዉ እንኳ ይህንን ተቀብለዉ ህዝባዊ ምላሽ የሚሰጡት ባለስልጣናት ቁጥር ኢምንት ነዉ፡፡ ምንም ይሁን ምን በህዝብ በኩል ጥያቄ ሲቀርብ መንግስት ህዝቡን ወርዶ በነፃነት አወያይቶ መፍትሔ ለመፈለግ አለመሞከር ኢ-ዲሞክራሲያነት ነዉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ቢሮክራሲያዊ ዉጣ ዉረዶች ታልፈዉ የክልሉ መንግስት ከወዲሁ ፍላጎቱ ባይኖረዉም የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሚያደርገዉ ህጋዊ ጫና የቅማንትን የማንነትና ራስ አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ አራት ጊዜ ጥናቶች እንዲካሄዱ አድርጓል፡፡

የመጀመሪያዉ ጥናት ሙሉ በሙሉ በክልሉ ካቢኔ የተጠና ሲሆን ፍፁም ገለልተኛ ያልሆነ የጥናት ዉጤት ይዞ ቀርቧል፡፡ የጥናቱ ዉጤት በክልሉ የተሻሻለዉ ህገ-መንግስት አንቀፅ 39(7) ስር ከተቀመጡት መስፈርቶች መካከል ቋንቋን እንደዋና መስፈርት በመዉሰድ ምንም ዓይነት ቅማንትኛ ቋንቋ ተናጋሪ እንደሌለ አድርጎ የቀረበ ሲሆን በሌሎች መስፈርቶች ላይም እዉነታ ላይ የተመሰረተ የጥናት ዉጤት አልቀረበም ነበር፡፡ በወቅቱ የጥናቱ ዉጤት በክልሉ ካቢኔ በኩል (ክቡር አቶ አያሌዉ ጎበዜ በተገኙበት) ቀርቦ ተተችቷል፡፡ የመጀመሪያዉ ትልቁ ትችት ጥናቱ ይዞት የቀረበዉ ዉጤት መሬት ላይ ካለዉ ሃቅ ጋር አይስማማም፤ ከእዉነታ የራቀ ነዉ የሚል ነበር፡፡ ሌላኛዉ መሠረታዊ ትችት ደግሞ ጥናቱን ያጠናዉ ቡድን ገለልተኛ የመሆን አቅም ያጥረዋል ቢያንስ የጥያቄዉ ባለቤቶች በሚካሄደዉ ጥናት ዉስጥ መሳተፍ ይገባቸዉ ነበር የሚል ነበር፡፡ አስተባባሪ ኮሚቴዉም ገና ከጅምሩ የመጀመሪያዉን ጥናት ለማጥናት የቅማንት ህዝብ ወደሚገኝበት አካባቢ ሲወጣ የአጥኚዉ ቡድን የአጠናን አካሄድ ግልፅነት የጎደለዉና የዲሞክራሲ መርህን የጣሰ እንደሆነ አስቀድሞ ለመንግስት በደብዳቤ አሳዉቆ ነበር፡፡ በመጨረሻም ከዉይይት በኋላ በተደረሰዉ ስምምነት የክልሉ መንግስት ጥያቄዉን ካቀረበዉ ብሔረሰብ ጋር በጋራ በመሆን ለሁለተኛ ጊዜ የማያዳግም ጥናት አካሂዶ የመጨረሻ እልባት እንዲሰጥ ነበር፡፡

ለሁለተኛ ጊዜ በተዋቀረዉ የጥናት ቡድን ዉስጥ አራት የቅማንት ምሁራን የተሳተፉ ሲሆን የጥናት ቡድኑ አባላት ወደ ጥናት መስክ ከመዉጣታቸዉ በፊት የጥናት ዕቅድ (research plan) በጋራ ነድፈዉና ተስማምተዉ ነበር፡፡ በመጀመሪያዉ የጥናት ዙር የቀረበዉን የጥናት ዉጤትና በዉይይት ወቅት የተደረሰበትን ስምምነት መሠረት በማድረግ በክልሉ የተሻሻለዉ ህገ-መንግስት አንቀፅ 39(7) ስር ከተቀመጡት መስፈርቶች መካከል ቋንቋና ባህልን ብቻ ማጥናት እንደሚያስፈልግ ሌሎች መስፈርቶች ግን ተጨማሪ ጥናት እንደማያስፈልጋቸዉ ተስማምተዉና ተፈራርምዉ ነበር፡፡ በስምምነታቸዉ መሠረትም ለጥናት ከተመረጡት ቀበሌዎች መካከል ቋራ ወረዳ ዉስጥ ሁለት ቀበሌዎችን መተማ ወረዳ ዉስጥ ደግሞ ሁለተኛዉ ቀበሌ (ሌንጫ) ላይ የጥናት መረጃ (research data) በመሰብሰብ ላይ እያሉ ያለምንም አጥጋቢ ምክኒያት የጥናት ቡድኑን በበላይነት ይመራ በነበረዉ ግለሰብ አማካኝነት የጥናት ሂደቱ ተቋርጧል፡፡ በወቅቱም ለጥናት ዓላማ ተሰብስቦ የነበረዉ ህዝብ (በቁጥር ከ60 በላይ) በአጥኚ ቡድኑ በኩል ተገቢዉን ምላሽና ክብር ባለማግኘቱ ቁጣዉን ገልፆም ነበር፡፡ የጥናት ሂደቱ ያለአግባብ በመንግስት ተወካዮች በኩል የተቋረጠ ስለመሆኑ የጥናት ቡድኑ አባላት የተፈራረሙበት ሰነድም ይመሰክራል፡፡ ለዚህ ሁሉ ችግር መንስኤዉ ደግሞ በመጀመሪያዉ የጥናት ዙር የጥናት ቡድኑ ሰብሳቢ የነበረዉ ግለሰብ አሁንም በሁለተኛዉ የጥናት ዙር በድጋሜ ሰብሳቢ መደረጉ ነዉ፡፡ በመጀመሪያዉ ዙር ጥናቱ ይዞት የቀረበዉ የጥናት ዉጤት በሁለተኛዉ ዙር የጥናት ዉጤት በከፍተኛ ደረጃ ዉድቅ እንደሚደረግ ሲገነዘብ የጥናት ዉጤቱን ከወዲሁ አቋርጦ መሄድ መርጧል፡፡ ይህ ደግሞ በዲሞክራሲ ዓይን ሲታይ የጥናት ቡድኑ ሰብሳቢ ተመሳሳይ ግለሰብ መሆኑ ቀርቶ ሌላ ገለልተኛ ሰዉ በመንግስት በኩል መመደብ ነበረበት፡፡ በመጨረሻም ከክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት (ክቡር አቶ በረከት ስምኦን በተገኙበት) ጋር በተደረገዉ ዉይይት ችግሩን በፈጠረዉ ሰብሳቢ ላይ ምንም ዓይነት ህጋዊ እርምጃ ሳይወሰድ ወይም የተቋረጠዉ ጥናት ከነበረበት ይቀጥል ሳይባል የብሔረሰቡ ተወላጆች እራሳቸዉ ብቻ አጥንተዉ ይቅረቡ የሚል ጫና የተሞላበት ሃሳብ ቀርቧል፡፡ ይሁን እንጂ የብሔረሰቡ ተወካዮች ይህንን ሃሳብ ገለልተኛ የመሆን መርህን መሠረት በማድረግ አጠንክረዉ የተቃወሙ ቢሆንም ተቀባይነት አላገኙም፡፡

ለሶስተኛ ጊዜ የብሔረሰቡ ተወካዮች እራሳቸዉ ጥናቱን አጥንተዉ ይዘዉ እንዲቀርቡ ሲደረግ መንግስት የጥናቱን ሙሉ ወጭ ሊሸፍን ነበር፡፡ ሆኖም መንግስት ከተደረሰዉ ስምምነት ዉጭ አቋም በመያዝ የጥናት ወጭ እንደማይሸፍን ገልፆ አስተባባሪ ኮሚቴዉ ቋንቋና መልክኣምድርን በተመለከተ ብቻ ማስረጃ ይዞ እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡ በዚህ የጥናት ዙር ወቅት አስተባባሪ ኮሚቴዉ ባለዉ ዉስን ሃብትና ጊዜ ተጠቅሞ በክልሉ የተሻሻለዉ ህገ-መንግስት አንቀፅ 39(7) ስር የተቀመጡትን የብሔረሰብነት መስፈርቶች የቅማንት ብሔረሰብ አሟልቶ እንደሚገኝ የሚያስረዱ ማስረጃዎችን በቅንነትና በታማኝነት አቅርቧል፡፡ ነገር ግን የቀረበዉ ጥናት ወይም ማስረጃ በተገመገመበት ወቅት የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት (ክቡር አቶ በረከት ስምኦንን ጨምሮ) የቀረበዉን ማስረጃ ወይም ጥናት ስሜት የተጫጫነዉ እና የተጋነነ ነዉ በማለት ዉድቅ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ የቀረበዉን ጥናት ተከትሎም በተደረገዉ ዉይይት በመንግስት ባለስልጣናት በኩል የቅማንትን ማንነት መካድ ትልቅ ታሪካዊ ስህተት መሆኑን አምነዉ ነገር ግን ራስ አስተዳደር ለመፍቀድ ሁሉም የቅማንት ብሔረሰብ ተወላጆች ቅማንትኛ ቋንቋ መቻል እንዳለባቸዉና በኩታ ገጠምነት መኖራቸዉ መረጋገጥ አለበት የሚል የተሳሳተ ህገ-መንግስታዊ ትርጓሜ ለመስጠት ሞክረዋል፡፡ ይህን የተሳሳተ ህገ-መንግስታዊ ትርጉም መሠረት አድርጎም የቅማንትኛ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ኩታ ገጠም አሰፋፈር ለማጥናትና የመጨረሻ ዉሳኔ ለመስጠት ለአንድ ወር ቀጠሮ ተይዞ ነበር፡፡

ይህን የመጨረሻ የዉሳኔ ግብዓት የሰ/ጎንደር ዞን ም/አስተዳደሪ (አቶ አማረ ሰጤ) ጉዳዩን በበላይነት ወስዶ ከቅማንት አስተባበሪ ኮሚቴ ጋር በጋራ አጥንቶ በተባለዉ ጊዜ ዉስጥ ለክልሉ መንግስት እንዲያቀርብ አቅጣጫ ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም ከተደረሰዉ ስምምነት ዉጭ ባልታወቀ ምክኒያት የክልሉ መንግስት እንደገና ለአራተኛ ጊዜ ሌላ አዲስ ጥናት እንዲካሄድ በጎን የጥናት ኮሚቴ አዋቀረ፡፡ አስተባባሪ ኮሚቴዉም አዲስ በተቋቋመዉ የጥናት ቡድን ዉስጥ በታዛቢነት ሊሳተፍ የሚችል አንድ ተወካይ ብቻ እንዲልክ በሰ/ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ (አቶ ግዛት አብዬ) በኩል ጥሪ የተደረገለት ቢሆንም አካሄዱ ከጅምሩ ቀደም ሲል የተደረሰዉን ስምምነት የጣሰ ነዉ በሚል እሳቤ እና ተሳትፎዉ ለይስሙላ ከመሆን አይዘልም በሚል ምክኒያት ራሱን አግልሏል፡፡

በኋላም አስተባባሪ ኮሚቴዉ የክልሉ መንግስት ራሱ ብቻ አጥንቶ ለቀረበዉ ጥያቄ የሚሰጠዉን ምላሽ በትዕግስትና በፅናት ጠብቆ ለማወቅ ተገዶ ቆይቷል፡፡ የክልሉ መንግስት ብቻዉን ለአራተኛ ጊዜ ያጠናዉን ጥናት ሰኔ 25 ቀን 2005 ዓ.ም በክልሉ ካቢኔዎች እና በብሔረሰቡ ተወካዮች ፊት ባቀረበበት ወቅት ከጥናቱ ዉጤትም ሆነ ዉይይት የተጠበቀ ምንም አዲስ ነገር ባይኖርም የቅማንት ማንነት በአዋጅ እንደሚመለስና የማንነቱ መገለጫ የሆኑት ቋንቋና ባህል ደግሞ በመንግስት ድጋፍ ሊጠበቁ እንደሚገባ ሃሳብ ከመሰጠቱም በተጨማሪ ቃልም ተገብቶ ነበር፡፡ የራስ አስተዳደርን በተመለከተ ግን ከዚህ በላይ በተጠቀሱት ምክኒያቶች ሊፈቀድ እንደማይችል ተደምድሟል፡፡ ይሁን እንጂ የአማራ ክልል ምክር ቤት በ4ኛ ዙር፣3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባኤ (ከሰኔ 29 እስከ ሐምሌ 5) በክልሉ ካቢኔ ለአራተኛ ጊዜ ተጠንቶ የቀረበዉን ጥናት መሠረት በማድረግ የራስ አስተዳደር መብቱን ቀርቶ ጭራሹኑ የቅማንትን የማንነት ጥያቄ ባግባቡ ያልመለሰ ዉሳኔ ሰጥቷል፡፡

4. የአብክመ ምክር ቤት ያስተላለፈዉ ዉሳኔ ዲሞክራሲያዊነትና ህጋዊነት

4.1. የስነ-ስርዓት ግድፈቶችና ምክር ቤቱ ስልጣንና ተግባሩን ባግባቡ ያልተወጣ ስለመሆኑ፤

የአብክመ ምክር ቤት እንደማኛዉም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በክልሉ የዉስጥ ጉዳዮች ላይ የበላይ የፖለቲካ ስልጣን ባለቤት ነዉ (አብክመ የተሻሻለዉ ህገ-መንግስት አንቀፅ 49(2))፡፡ በአብክመ ህገ-መንግስት የተሰጡት ሌሎች ስልጣኖች እንደተጠበቁ ሆኖ የፌዴራሉን ህገ-መንግስት የማይፃረሩ ህጎችን የማዉጣት ስልጣን አለዉ (አብክመ የተሻሻለዉ ህገ-መንግስት አንቀፅ 49(3)(1))፡፡ የህዝቡን ብዛት፣ የክልሉን ስፋትና ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ግምት ዉስጥ በማስገባት በክልሉ ዉስጥ ተጨማሪ የአስተዳደር እርከኖችን ወይም የራስ በራስ አስተዳደራዊ አካባቢዎችን የማቋቋም ኃላፊነትና ስልጣን አለዉ (አብክመ የተሻሻለዉ ህገ-መንግስት አንቀፅ 49(3)(2))፡፡ የክልሉን ርዕሰ መስተዳድርና ሌሎች የክልሉን መንግስት ባለስልጣናት ለጥያቄ የመጥራትና የአስፈፃሚዉን አካል አሠራር የመመርመር ኃላፊነትና ስልጣን አለዉ (አብክመ የተሻሻለዉ ህገ-መንግስት አንቀፅ 49(3)(17))፡፡

ከዚህ በላይ ከተጠቀሱት ህገ-መንግስታዊ ስልጣኖችና ኃላፊነቶች በተጨማሪ የአንድ ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ህዝብ የማንነት ጥያቄ ሲነሳ የክልሉ ምክር ቤት በመጀመሪያ ደረጃ የማየት ስልጣንና ኃላፊነት እንደሚኖረዉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የስልጤ ብሔረሰብ የማንነት ጥያቄን በመለሰበት ወቅት በአብላጫ ድምፅ ዉሳኔ አስተላልፏል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚሰጣቸዉ ዉሳኔዎች ደግሞ የአስገዳጅነት ባህርይ እንዳለቸዉ አዋጅ ቁጥር 251/1993 በግልፅ ይደነግጋል (አንቀፅ 11)፡፡ ስለሆነም የቅማንትን የማንነትና ራስ አስተዳደር ጥያቄ ተገቢዉን ጥናት አስጠንቶ ህጋዊ ምላሽ የመስጠት ኃላፊነትና ስልጣን የሚኖረዉ ዋናዉ የመንግስት ተቋም የአብክመ ምክር ቤት ነዉ፡፡ ይሁን እንጂ በተግባር እንደታየዉ የቅማንትን የማንነትና ራስ አስተዳደር ህገ-መንግስታዊ ጥያቄ በበላይነት ይዞ ጥናት መካሄድ አለበት በሚል ምክኒያት ያለአግባብ ህጉ ካስቀመጠዉ የጊዜ ገደብ ዉጭ ሲያዘገየዉ የቆየዉ የክልሉ አስፈፃሚ አካል (ካቢኔ) ነዉ፡፡ የክልሉ ምክር ቤት የቅማንትን የማንነትና ራስ አስተዳደር ጥያቄ በተመለከተ ህጉ ከሚያስቀምጠዉ ግዴታ አንፃር የአንበሳዉን ድርሻ ወስዶ ጥናቱ ባግባቡ እንዲካሄድ አድርጓል ለማለት በፍፁም አይቻልም፡፡ ሌላዉ ቢቀር አስፈፃሚዉን አካል (ካቢኔዉ) በበላይነት የመቆጣጠር ሚናዉን በህጉ አግባብ ተወጥቷል ለማለትም አያስደፍርም፡፡

የአብክመ ምክር ቤት በአስፈፃሚ አካሉ (በካቢኔዉ) ተጠንቶ የቀረበለትን ጥናት እና በህግ፣ፍትህና አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ በኩል የቀረበለትን የዉሳኔ ሃሳብ መሠረት አድርጎ ብቻ የቅማንት ብሔረሰብ
የማንነትና ራስ አስተዳደር ጥያቄ በክልሉ የተሻሻለዉ ህገ-መንግስት አንቀፅ 39(7) ስር የተመለከቱትን መስፈርቶች ስለማያሟላ የራስ አስተዳደር ሊፈቀድ አይገባም በማለት በአብላጫ ድምፅ ወስኗል፡፡ የክልሉ ምክር ቤት ከራስ አስተዳደር ዉጭ የተነሳዉን የቅማንት የማንነት ጥያቄ የመለሰ ይምሰል እንጂ አጠቃላይ የዉሳኔዉ ይዘት ሲመረመር የማንነት ጥያቄዉ ተድበስብሶ ዉሳኔ የተሰጠበት ነዉ፡፡

የቀረበዉ የማንነትና ራስ አስተዳደር ጥያቄ ዉሳኔ ባገኘበት ሃምሌ 03 ቀን 2005 ዓ.ም በክልሉ ምክር ቤት ዉስጥ የተካሄደዉ ክርክር ወይም ዉይይት አግባብና ጥልቀት የነበረዉ መሆኑን በተሰጠዉ ዉሳኔ ቢገልፀም በተቃራኒዉ በምክር ቤቱ ዉስጥ የቅማንት ጉዳይ በታየበት ከላይ በተጠቀሰዉ ቀን የነበረዉ የዉይይትና ክርክር ስርዓት እጅግ ኢ-ዲሞክራሲያዊና አድሎኣዊ የተሞላበት ነበር፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የዉይይቱ ወይም የክርክሩ ኢ-ዲሞክራሲያዊነትና አድሎኣዊነት ይኸዉ ዉይይት ወይም ክርክር ለህዝብ ይፋ እንዳይሆን ከመከልከሉ ይጀምራል፡፡ ምክር ቤቱ በ4ኛ ዙር፣3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባኤ (ከሰኔ 29 እስከ ሐምሌ 5) በአጀንዳ ይዞ ዉይይት ወይም ክርክር ያደረገባቸዉን ጉዳዮች በቀጥታ ለህዝብ ይፋ ያደረገ ሲሆን በቅማንት የማንነትና ራስ አስተዳደር ጥያቄ ዙሪያ የተካሄደዉ ዉይይት ወይም ክርክር ለህዝብ ይፋ እንዳይሆን ተደርጓል፡፡ ይህ ጉዳይ ደግሞ በምክር ቤቱ አባላት መካከል የተካሄደዉን የሃሳብ መንሸራሸር የቅማንት ህዝብም ሆነ ሌላዉ ህዝብ በቀጥታ እንዳይገመግም ዕድል ነፍጎታል፡፡ ህዝብ የተወከለባቸዉ ምክር ቤቶች የሚያደርጓቸዉን ክርክሮች ወይም ዉይይቶች ለህዝብ በቀጥታ ማስተላለፍ የግልፅነትና ተጠያቂነት የዲሞክራሲያዊ መርሆች በተግባር የሚገለፁበትን መንገድ የመፍጠር ዓላማ አለዉ፡፡ ህዝብ የወከላቸዉ የምክር ቤት አባላት የሚወስኗቸዉ ህዝባዊ ዉሳኔዎች ፍትሃዊና የህዝቡን ጥቅም የሚያስጠብቁ መሆናቸዉ የሚረጋገጡት በዚህ ዲሞክራሲያዊ መንገድ ነዉ፡፡

በእርግጥ አንዳንድ የምክር ቤት ዉይይቶችና ክርክሮች ለህዝብ ይፋ የማይሆኑበት የተለዬ ህጋዊ አግባብ ይኖራል፡፡ የአብክመ የተሻሻለዉ ህገ-መንግስት እንደሚያስቀምጠዉ የክልሉ ምክር ቤት ስብሰባ በዝግ እንዲካሄድ በምክር ቤቱ አባላት ወይም በክልሉ አስፈፃሚ አካል ከተጠየቀና ከምክር ቤቱ አባላት መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ጥያቄዉን ከደገፉት ምክር ቤቱ ዝግ ስብሰባ ሊያደርግ እንደሚችል ነዉ (አንቀፅ 54(5))፡፡ ይሁን እንጂ የቅማንት የማንነትና ራስ አስተዳደር ጥያቄ በምክር ቤቱ ዝግ ስብሰባ እንዲወሰን አንድም ጥያቄ አልቀረበም፤የምክር ቤት አባላትም በዚህ ጉዳይ ድምፅ አልሰጡበትም፡፡ ስለሆነም የቅማንት ጉዳይ ህጉ ከሚያዘዉ ዉጭ በዝግ ስብሰባ ዉይይት ወይም ክርክር መወሰኑ መሠረታዊ የህግ ስነ-ስርዓት ችግር የነበረበትና የዲሞክራሲን መርህ ያልተከተለ መሆኑን ነዉ፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የአብክመ ምክር ቤት የቅማንትን ጉዳይ ሲወስን በጣም በተጣበበና ለዉይይት ወይም ለክርክር ሰፊ ዕድል በነፈገ ስነ-ስርዓት ነዉ፡፡ የቅማንት ጉዳይ ለምክር ቤት አባላት ለዉይይት ወይም ለክርክር የቀረበዉ ከ10፡00-11፡30 ሠዓት (ከሠዓት በኋላ) በሆነበት ጊዜ ነበር፡፡ የማንነትን ጥያቄ በዚች አጭር ጊዜ ሰፊ ዉይይት ሳይካሄድበት ተሯሩጦ መወሰን አካሄዱ ምን ያህል ኢ-ዲሞክራሲያዊ እንደነበር መረዳት አያዳግትም፡፡ በርካታ የምክር ቤት አባላት የተቃዉሞ ድምፅ ለማሰማት እጃቸዉን እያወጡ በግልፅ ዕድል ተነፍጓቸዉ በጉዳዩ ዙሪያ ሰፊ ዉይይት ወይም ክርክር ሳይካሄድ ያለአግባብ የእነ ተሎ ተሎ ቤት ዉሳኔ ተሰጥቷል፡፡ የቅማንት አስተባባሪ ኮሚቴም በታዛቢነት በምክር ቤቱ እንዲሳተፍ ዕድሉ ያልተሰጠዉ ቢሆንም በበኩሉ የቅማንትን ህዝብ የወከሉትን የምክር ቤት አባላት ሰብስቦ በማወያየት ስለነበረዉ የምክር ቤት የዉሳኔ አሰጣጥ ስነ-ስርዓት ለመረዳትና ማስረጃ ለመሰብሰብ ምክሯል፡፡ ሂደቱ ባጠቃላይ ህግንና የዲሞክራሲን መርህ ያልተከተለ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ የሚያሳየዉ የፌዴራሉ ህገ-መንግስት ለብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሰጠዉን ከፍተኛ ቦታ የሚያሳንስና በአጠቃላይ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ለቅማንት የማንነትና ራስ አስተዳደር ጥያቄ አወንታዊ ምላሽ ላለመስጠት ከጅምሩ አንስቶ ያሳየዉን ትልቅ ፍላጎት የክልሉ ምክር ቤት በግልፅ ያንፀባረቀበት የዉሳኔ ሂደት መሆኑን ነዉ፡፡

4.2. የቅማንት የማንነትና ራስ አስተዳደር ጥያቄ ከህገ-መንግስቱ መስፈርቶች አንፃር ሲታይ፤
የአንድ ማህበረሰብ የማንነት ጥያቄ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብቶች መሠረትና ምንጭ በመሆኑ ከፍተኛ ግምት ሊሰጠዉ እንደሚገባ የፌዴራሉ ህገ-መንግስት አጣሪ ጉባኤ የስልጤን የማንነት ጥያቄ ለመፍታት የህገ-መንግስት ትርጉም በሰጠበት ወቅት አፅንኦት ሰጥቷል፡፡ ስለሆነም የማንነትና የራስ በራስ ማስተዳደር ጥያቄ ባንድ ላይ በአንድ ማህበረሰብ ሲነሱ መጀመሪያ የማንነት ጥያቄዉ በግልፅ መመለስ አለበት፡፡ ማንነት የራስ አስተዳደር መሰረት ነዉ፡፡ ቋንቋ፣ባህልና ሃይማኖት የማንነት ዋና መገለጫዎች ናቸዉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ያለማንነት ሊቆሙ አይችሉም፡፡

የቅማንት ህዝብ ከጥንት ጀምሮ ራሱን ከሌላዉ ህዝብ (ከአማራዉ) ለይቶ የሚያይበት የጎሳ ማንነት አለዉ (ethnic identity)፡፡ በአካባቢዉ የሚኖሩ የአማራ ጎሳ አባላትም የቅማንትን ህዝብ በጎሳ የተለዩ እንደሆኑ በማህበራዊም ሆነ በፖለቲካ እንቅስቃሲያቸዉ የሚያሳዩበት አረዳድና አቀባበል ጎልቶ ይታያል፡፡ ይህ በተለይ አድሎኣዊ ተግባር ለመፈፀም ሲባል ቅማንቶችን በጎሳ ማንነታቸዉ ማግለል (an act of marginalization on the basis of their ethnic identity) የተለመደ ነዉ፡፡ ቀደም ሲል የጠቀስናቸዉ በቅማንት ህዝብ ላይ ከድሮ ጀምሮ ስር ሰደዉ የቆዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በዋናነት በቅማንት የጎሳ ማንነት ላይ ያነጣጠሩ ናቸዉ፡፡ የቅማንት ህዝብ በከፍተኛ ደረጃ በኢኮኖሚ፣በፖለቲካ፣በማህበራዊና ባህላዊ ህይወቱ ላይ እየገጠመዉ ያለዉ አግላይና አድሎኣዊ አስተዳደር (marginalizing and discriminatory administration) ዋና ምንጩ የጎሳ ማንነቱ (የቅማንት ማንነቱ) ከአማራዉ ህዝብ የተለየ መሆኑ ነዉ፡፡ ይህ ደግሞ በቀላሉ የማይጠፋና ልዩነቱ ታሪካዊ ይዘት ያለዉ ነዉ፡፡ የታሪክ ሰነዶች፣የጥናትና ምርምር ዉጤቶችና የታሪክ አባቶች እንደሚያስረዱት እስከ ደርግ ዘመነ መንግስት ድረስ በአማራና ቅማንት ጎሳዎች መካከል (በተለይም በሚኖሩባቸዉ ደንበር አካባቢዎች) ደም አፋሳሽ ግጭቶችና የንብረት ዘረፋ ድርጊቶች ይፈጠሩ እንደነበር ነዉ፡፡ አሁንም ቢሆን አልፎ አልፎ ጎሳን መሠረት ያደረጉ ግጭቶችና የንብረት ዘረፋ ወንጀሎች እንደሚከሰቱ ማሳያ ማስረጃዎች አሉ፡፡

አብላጫ ቁጥር ያለዉ የአማራ ጎሳ (majority Amhara) በአንፃራዊነት አናሳ ቁጥር ያለዉን የቅማንት ጎሳ (minority Kemant) ዉጦ በኃይል የማንነት ለዉጥ (forceful assimilation or forceful identity conversion) ለማምጣት ከጥንት አንስቶ እስከአሁኑ ዘመን ድረስ ስራዉን እየሰራ ነዉ፡፡ ህዝቡን አስገድዶ በአማራ ጎሳ ስም በህዝብና ቤቶች ቆጠራ ወቅት እንዲቆጠር መደረጉ ለአብነት የሚጠቀስ ተግባር ነዉ፡፡ ይሁን እንጂ የቅማንት ጎሳ ልክ እንደ አማራ ጎሳ በስሙ በማንኛዉም መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋሞች መመዝገብና የጎሳ ማንነቱ እንዲታወቅለት ይፈልጋል፡፡ አማራ መሆን ምርጫ እንጂ ግዳጅ የሚሆንበት ምንም ዓይነት ሳይንሳዊም ሆነ ህጋዊ ምክኒያት የለም፡፡

የክልሉ መንግስት ያጠናዉን ጥናት መሠረት አድርጎ በቅማንት ጉዳይ ላይ ዉሳኔ ሲሰጥ ማንነት ላይ ላይ ትኩረት አልሰጠም፡፡ ትኩረት ያደረገዉ በማንነቱ መገለጫዎች (ቋንቋና ባህል) እና በራስ አስተዳደር ጥያቄዉ ላይ እንጅ የእነዚህ ሁሉ መሠረት ስለሆነዉ የቅማንት የጎሳ ማንነት (related ethnic identity) የክልሉ መንግስት ትኩረት አልሰጠም፡፡ በአብክመ የተሻሻለ ህገ-መንግስት አንቀፅ 39(7) ስር ከተቀመጡት የብሔረሰብ እዉቅና መስፈርቶች መካከል የህዝቦች በጋራ ወይም በተዛመደ ህልዉና (related identity) ማመናቸዉ ነዉ፡፡ ቅማንቶችን ከጥንት ጀምሮ በጋራ የሚያዛምዳቸዉ እና የጋራ ህልዉና አለን ብለዉ የሚያምኑበት የጎሳ ማንነታቸዉ (related ethnic identity) ነዉ፡፡ የቅማንት ህዝብ በጎሳ ማንነቱ ሳያፍርና ሳይሸማቀቅ በይፋ እንዲታወቅ ይፈልጋል፡፡ በጎሳ ማንነቴ ስም ልቆጠር ልጠራ እንጅ በአማራ የጎሳ ማንነት ስም ልቆጠርና ልጠራ አይገባም በሚል እሰጥ አገባ ዉስጥ ይገኛል፡፡ የቅማንት ህዝብ የጋራ የስነ ልቦና አንድነት (a common psychological make up) ባሁኑ ወቅት ጫፍ ላይ የደረሰ ነዉ፡፡

የክልሉ መንግስትም የቅማንት ህዝብ የተዛመደ ወይም የጋራ ህልዉና አለኝ ብሎ እንደሚያምን የተስተዋለ መሆኑንና የጋራ የስነልቦና አንድነት እንዳለዉ ማረጋገጡን ምክር ቤቱ በሰጠዉ ዉሳኔ ላይ መረዳት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ የክልሉ መንግስት የቅማንትን የጎሳ ማንነት ልክ እንደሌሎች የህግ እዉቅና እንዳገኙ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የህግ እዉቅና (የአዋጅ እዉቅና) እንዲያገኝ የሚያስችል ዉሳኔ አልሰጠም፡፡ ይህ ካልሆነ ግን አሁንም ቢሆን የቅማንት የማንነት ጉዳይ እንደድሮዉ ይፋ ሳይወጣ በሹክሹክታ ይቀጥላል ማለት ይሆናል፡፡ በህዝብ ቆጠራ ወቅት ቅማንት ብሎ መመዝገብ አይኖርም፡፡ ባጠቃላይ በመንግስት ተቋማትም ሆነ በግል ድርጅቶች በሚደረጉ ህጋዊ ዉጤት ባላቸዉ ምዝገባዎችና ሰነዶች ላይ የቅማንት ስም አይሰፍርም ማለት ነዉ፡፡ የአማራ ክልል መንግስትም ሆነ የአማራ ህዝብ የቅማንት የጎሳ ማንነት እዉቅና እንዲያገኝ ከጥንቱም ፍላጎት የለዉም፡፡ ይፋ የሆነ ህጋዊ እዉቅና እስከሌለ ድረስ ሚዲያዎችም ቢሆን የቅማንትን ጉዳይ በተመለከተ ሳይፈሩ ስሙን አንስተዉ መዘገብና ማሰራጨት አይችሉም፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ የክልሉ ምክር ቤት በቅማንት ጉዳይ ላይ ያስተላለፈዉ ዉሳኔ ሲገመገም የቅማንትን ማንነት አድበስብሶ አልፎታል ያሰኛል፡፡ የክልሉ መንግስት ቅማንት የሚባል ህዝብ ወይም ጎሳ የለም የሚል ዉሳኔ አላስተላለፈም፡፡ የቅማንት ጎሳ ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያ ዉስጥ የነበረ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ይሁን እንጂ ያለህግ እዉቅና (de facto recognition) እንደድሮዉ እንዲቀጥል ወስኗል፡፡ የቅማንት ማንነት የህግ እዉቅና ( de jure recognition) ያስፈልገዋል፡፡ ስለማንነት አስፈላጊነት ጉዳይ የፌዴሬሽን ም/ቤት በስልጤ የማንነት ጉዳይ ላይ የሰጠዉን ዉሳኔ በጥልቀት መመልከቱ የቅማንትን ማንነት ጉዳይ ባግባቡ ��

Notice:
Neither do articles published on this site necessarily reflect an editorial policy of the WLKA nor its position on issues expressed by respective authors.

Advertisements
This entry was posted in Agaw Kemant. Bookmark the permalink.

6 Responses to ‘Legitimacy’ of ANRS Council’s Decision on Kemant’s Quest for Recognition and Self-Rule

 1. Ad says:

  NOTE TO THE AUTHOR:
  Please write your article in English in the future. Because Amharic characters take much space(kbs) and there is no guarantee for publication of your article.

 2. Baalya says:

  As the new generation, some us in Diaspora do not know Amharic, someone proficient in English language can translate this article please?

 3. Saba says:

  Plese forward the PDF form of the article; some of us can’t read the saba-letter in such form!

 4. TATEKENDEGENA says:

  TILAHUN
  YOU SAID THESE
  “የአማራ ህዝብ የቅማንት የጎሳ ማንነት እዉቅና እንዲያገኝ ከጥንቱም ፍላጎት የለዉም”
  mengistachihun teyiku.
  i strongly advice you is please don’t blame the people.
  the Amara people has huge number of enemies. why you blame the poor people?

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s